(ህዳር 9/2017 ዓ.ም) በፓናል ውይይቱ መክፈቻ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግስት ከፀደቀ ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በትምህርት ተቋማት ሲከበር መቆየቱን አውስተው የዘንድሮው በዓል አከባበርም በትምህርት ተቋማት በተለያዩ የፓናል ውይይቶች ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል::
አማካሪዋ እንዳሉት በትምህርት ቤቶች ሲደረጉ በቆዩ ፓናል ውይይቶች ተማሪዎች ህብረብሔራዊ አንድነትና አብሮነትን ለማጎልበት የሚያስችል ግንዛቤ እንዲይዙና ወደ ተግባር እንዲገቡ ሰፊ አቅም የሚፈጥር እንደነበር አብራርተዋል:: አክለውም ልዩነታችን ህብረብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን በመረዳት አብሮነታችንን ለማጠናከር የሚረዱ ሃሳቦች በማጠቃለያ ውይይቱ በማንሳት ባህልና ቋንቋን በመጋራት የሀገራችንን አብሮነት የሚያጠነክሩ ተማሪዎች እንድናፈራ በጋራ መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ በበኩላቸው ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የብዙዎችን ሕይወት ዋጋ ያስከፈለ ጊዜ ማለፉን አስታውሰው ከነጠላ ትርክቶች በመውጣት ሀገራዊ መግባባት በመፍጠር ህብረብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከርና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የትምህርት ተቋማት ኃላፊነት መሆኑን መረዳት እንደሚገባ አብራርተዋል:: አያይዘውም አብሮነት አንድነትን እንደሚያጠናክር በመረዳት ሁሉም በማንነቱ በመኩራት ሀገራችንን የማሳደግ ኃላፊነታችንን እንወጣ በማለት አሳስበዋል::
በፓናል ውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ፣ የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ፣ የወተማ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሐሰን ሺፋ እና የቢሮ አጠቃላይ ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የቢሮው የስነ ምግባር መሻሻልና የተማሪዎች ጉዳይ ባለሙያ በሆኑት አቶ ባይሳ ፀጋዬ በሕብረ ብሔራዊ ፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች እና የመፍትሄ ሃሳቦች የያዙ ሁለት ሰነዶች አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ለ19 ጊዜ “ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት!” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ሲያካሂድ የነበረውን የፓናል ውይይት በዛሬው እለት አጠናቀቀ፡፡
0 Comments