(ሀምሌ 16/2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር የምዝገባ ሂደቱን አስመልክቶ ከኢቲ ቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የ2017 ዓ.ም የተማሪዎች ምዝገባ ኦን ላይን እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመው ከምዘገባ ሂደቱ ጋር በተገናኘ ቢሮው ከኢኖ ቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ርዕሳነ መምህራንን ጨምሮ ምዝገባውን ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አስታውቀዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም ለኦንላይን ምዝገባው ምንም አይነት ክፍያ የማይጠየቅ በመሆኑ ወላጆች ይህንን ተገንዝበው ልጆቻቸውን ያለምንም ክፍያ ማስመዝገብ እንደሚገባቸው ጠቁመው ከዚህ ተቃራኒ በሆነ አሰራር ለምዝገባው ክፍያ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶች ካሉ አስፈላጊውን የተጠያቂነት ስርአት የማስፈን ስራ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
የኦንላይን ምዝገባው ለተጨማሪ 15 ቀናት የተራዘመ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ተረጋግተው እንዲያስመዘግቡ እና ተማሪዎቹ ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የመማሪያ መጽሀፍ መውሰድ እንደሚገባቸው ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስረድተዋል።
0 Comments