ቢሮው በ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ አመት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ያከናወናቸውን የቅንጅታዊ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ተግባራት አፈጻጸም ገመገመ።

by | ዜና


(ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም) በመርሀ ግብሩ ከቢሮው ጋር በትስስር የተለያዩ ተግባራት ከሚያከናውኑ ተቋማት የመጡ ኃላፊዎችና ተወካዮችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም በትምህርት ሴክተሩ የድጋፍና ክትትል ተግባር የሚያከናውኑ የፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ፣የከንቲባ ጽህፈት ቤት እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ቡድን መሪ አቶ ሀፍቱ ብርሀኑ በ1ኛ ሩብ አመት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ የተከናወኑ የቅንጅታዊ አሰራርና መልካም አስተዳደር ተግባራት አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እያከናወነ በሚገኘው ተግባር በርካታ ውጤታማ ስራዎች መሰራታቸውን ጠቁመው የ2017 ዓ.ም 1ኛ ሩብ አመት በትምህርት ሴክተሩ የዝግጅት ምዕራፍ ተግባራት የተከናወኑበት ወቅት እንደመሆኑ የዛሬው መርሀ ግብር ተቋማቱ እንደየድርሻቸው የነበራቸው አስተዋጽኦ ተገምግሞ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።

ዶክተር ዘላለም አያይዘውም በቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ ተግባራት ከሚከናወንባቸው ሴክተሮች መካከል አንዱ እና ዋነኛው የትምህርት ሴክተሩ እንደመሆኑ ባለድርሻ አካላት ከቢሮው ጋር በጋራ በመሆን ሀገር ተረካቢ ዜጋ በማፍራት ሂደቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶችና ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር በቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ ስራ ከሚያከናውኑ ሴክተሮች መካከል ትምህርት ቢሮ ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸው በአንደኛ ሩብ አመት በትስስር የተከናወኑ ውጤታማ ስራዎችን በማጠናከርና በሂደት የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች በቀረበው የአንደኛ ሩብ አመት የቅንጅታዊ አሰራር አፈጻጸም ሪፖርት ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበው በቢሮው የማኔጅመንት አባላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰቷል።

0 Comments