በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የእውቅና ፈቃድ እንደሚሰጥ ተገለፀ፡፡

by | ዜና

(ቀን ሚያዚያ 1/ 2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን በጋራ በመሆን ለመንግስት ትምህርት ተቋማት እውቅናና ፈቃድ ለመስጠት በተደረገ የምዘና ውጤት ሪፖርት ላይ ውይይት አካሄደዋል ::

በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላት ፣ የትምህርትና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣ  ኃላፊዎችና በሁሉም ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የሚገኙ የጽ/ቤት ሀላፊዎች፣ የክፍለ ከተማ ትምህርት ፅ/ቤት ኃላፊዎች ፣  የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዋናና ምክትል ርእሳነ መምህራንና ክላስተር አስተባባሪዎች ፣ የክፍለ ከተማ ስራ መሪ አስተባባሪዎች እንዲሁም የቢሮ ዳይሬክቶሬቶች ተሳታፊ ሆነዋል ::

የትምህርት ስልጠና ጥራት ቁጥጥር  ባለስልጣን የመንግስት ትምህርት ቤቶችን በግብአት ፣ ሂደትና ውጤት በመመዘን ለዜጎች ጥራት ያለው ትምህርት በማቅረብ ውጤታማ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችል የእውቅና ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ  ማዘጋጀቱን  በመድረኩ ላይ ተግልጻል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ዑመር ለትምህርት ጥራትና የተሻለ ውጤት የትምህርት አመራሩ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው  ቀደም ሲል በተደረገ ምዘና የታዩ ጉድለቶችን በማረምና መልካም አጋጣሚዎችን በዝርዝር በማየት ቼክሊስቱ የሚጠይቀውን ለማሟላት በጋራ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል:: የትምህርት ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላትም የትምህርት ስራው የሚፈልገውን ትጋት በመረዳት በተሻለ ተነሳሽነትና የማስተዳደር አቅም በመፍጠር መስራት እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል ::

የአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ ዳኛው ገብሩ በምዘና ሂደቱ አጥጋቢ ውጤት ያላመጣ ትምህርት ቤት በድጋሚ እንደሚመዘን አብራርተዋል::  የትኛውም የመንግስት ትምህርት ቤት እውቅና ፈቃድ ሳያገኝ እንዳይቀር የትምህርት ተቋማትና አመራሩ በጋራ በመደጋገፍ ለዳግም ምዘና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል ::

አቶ ዳኛው አክለውም ከእውቅና ፈቃዱ ባለፈ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቁ ዜጋ የማፍራት ተልእኳችንን በአግባቡ መወጣት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል ::

የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ደቻሳ በበኩላቸው ለመንግስትና ለግል ትምህርት ቤቶች የተዘጋጀው ስታንዳርድ ተመሳሳይ መሆኑን በመረዳት የመንግስት ትምህርት ቤቶችን በበቂ ሁኔታ በግብአት ፣ ሂደትና ውጤት በማደራጀት የትምህርት ጥራትን በጋራ ልናረጋግጥ ይገባል ብለዋል :: አያይዘውም ትምህርት ቤቶች የምዘና ግብረ መልሱን በማየት የታዩ ጉድለቶችን በማረም ለቀጣይ ምዘና  ዝግጅት እንዲያደርጉ አሳስበዋል ::

 

0 Comments

SITE VISITORS

  • 1
  • 63
  • 486
  • 1,624
  • 7,586
  • 236,282
  • 236,282