የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሚዲያ ይዘት ማበልጸግና ስርጭት ዳይሬክቶሬት በክፍሉ ለሚገኙ ፕሮግራም አዘጋጆችና ቴክኒሺያኖች በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጠ።

by | ዜና

(ታህሳስ 9/2017 ዓ.ም) ስልጠናው በዋናነት በድምጽ አርትኦት (Audio Editing)) ፣ በፕሮግራም አዘገጃጀትና በሌሎች መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ጽንሰ ሀሳብና አሰራሮች ዙሪያ የተዘጋጀ ሲሆን ስልጠናው በስራ ክፍሉ በሚገኙና በዘርፉ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች ነው የተሰጠው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሚዲያ ይዘት ማበልጸግና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ የውብዳር አያሌው በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በስራ ክፍሉ የሚገኙ የፕሮግራም አዘጋጆችም ሆኑ የቴክኒክ ባለሙያዎች በዚህ የክህሎት ማሻሻያ ስልጠና አማካይነት በሚያገኙት ዕውቀት መነሻ ተቀራራቢ ግንዛቤ ፈጥረው ተቋሙን ውጤታማ ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ጠቁመው ስልጠናው ከንድፈ ሀሳብ ባሻገር በተግባር ተደግፎ እንደመሰጠቱ ባለሙያዎቹ በስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ መሰረት በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

የሚዲያ ይዘት ማበልጸግና ስርጭት ጣቢያ ሀላፊ አቶ አብይ ተፈራ በበኩላቸው ስራ ክፍሉ ቀደም ሲል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በዳይሬክቶሬቱ ለሚገኙ ባለሙያዎች የክህሎት ማሻሻያ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸው የዛሬው ስልጠና በክፍሉ የሚገኙ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ለባልደረቦቻቸው ያላቸውን ዕውቀት በአግባቡ ማካፈል እንዲችሉ ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

የድምጽ አርትኦት (Audio Editing) የምናዘጋጃቸው ፕሮግራሞችን በምንፈልገው መልኩ በጥራት መጠቀም እንድንችል የሚያግዝ መሆኑን በሚዲያ ይዘት ማበልጸግና ስርጭት ዳይሬክቶሬት የፕሮግራም አዘጋጅ የሆኑት አቶ አክመል ሙስጠፋ ከድምጽ አርትኦት (Audio Editing) ጋር በተገናኘ ስልጠና በሰጡበት ወቅት ገልጸዋል፡፡

0 Comments