ከቁለፍ አፈጻጸም አመላካች እቅድ እና ሪፖርት አስተዳደር ስርዓት (key performance indicater planning and reporting management system) አተገባበር ጋር በተገናኘ በተግባር የተደገፈ ስልጠና ተሰጠ፡፡

by | ዜና

(ታህሳስ 3/2017 ዓ.ም) ስልጠናው ለቢሮው አላማ ፈጸሚ ዳይሬክቶሬቶች ቀደም ሲል በፕላን ኮሚሽን እና በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አማካይነት የተሰጠ ተመሳሳይ የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ የቢሮው ባለሙያዎች ነው የተሰጠው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ከተማ አስተዳደሩ በቴክኖሎጄ የተደገፈ የእቅድ እና ሪፖርት ስርአት በማስፈን ለተገልጋዩ ወጥ የሆነ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ በማሰብ ቀደም ሲል በፕላን ኮሚሽን እና በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ አማካይነት ከሁሉም ተቃማት ለተወጣጡ አካላት የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመው የቢሮው አላማ ፈጸሚ ዳይሬክቶሬቶች በሲስተሙ መሰረት የ2017ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ መረጃዎችን ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

የቢሮው የእቅድና በጀት ዝግጅት ግምገማና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ለማ በበኩላቸው ሲስተሙ አላማ ፈጻሚ ስራ ክፍሎች የቁልፍ አመላካች እቅዳቸውን እና ሪፖርታቸውን ወደ ሲስተሙ በማስገባት ግልጽ የሆነ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃ ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ የሚያግዝ መሆኑን ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት አመላክተዋል፡፡

ሲስተሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ኮሚሽን በሚያስተዳድረው www.planreport.gov.et ዌብ ሳይት አማካይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኢኮቴ መሰረተ ልማት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ታዬ ወልደኪዳን ገልጸዋል፡፡

0 Comments