ኤች አይቪ ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር ላይ በትኩረት እንዲሰራ ተጠየቀ::

by | ዜና

(ጥቅምት 16/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ትግበራ ቡድን ኤች አይቪ ኤድስን መከላከልና መቆጣጠር መሰረት ያደረገ ክትትልና ድጋፍ ውጤት ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የጋራ ውይይት አድርጓል ::

በውይይቱ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክተር ወ/ሮ በላይነሽ የሻው የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመገንዘብ በሚቀርበው ሪፖርት ላይ የሚታዩ ጠንካራ ጎኖችን አጠናክሮ በመቀጠል የታዩ ክፍተቶች ላይ በትኩረት መስራት የውይይቱ ተሳታፊዎች ዋና ሥራ መሆን አለበት ብለዋል :: ዳይሬክተሯ አክለውም ኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶ የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ርእሳነ መምህራን በግምገማ ሂደት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል ::

የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያዋ ገንዘብ ደሳለኝ በበኩላቸው ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ሥራዎችን ያሉበትን ደረጃ ለማየት በ2016 ዓ.ም ማጠቃለያ በ250 አንደኛ ደረጃና 79 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ክትትልና ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው በድጋፍና ክትትሉ የተገኙ ውጤቶች በኤች አይ ቪ መከላከል ስራው ላይ በቂ ምላሽ ባለማሳየታቸው ይህን ውጤት መነሻ በማድረግ ትምህርት ቤቶች በፀረ ኤድስ ክበባት የሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ይጠበቃል ብለዋል ::

ባለሙያዋ የአለም ፀረ ኤድስ ቀንን ጠብቆ ከማስተማር በዘለለ መምህራን በስርአተ ትምህርቱ የተካተቱ ርዕሶች ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩና ክበባትም የየእለት ግንዛቤና ማስረፅ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ጠይቀው ተግባራዊነቱን ለማየት የስራ ክፍሉ በየሩብ ዓመቱ በቼክ ሊስት የተደገፈ ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል ::

በውይይቱ የትምህርት ቤቶች ፀረ ኤድስና ጤና አጠባበቅ ባለሙያዎች ፣ ዘርፉን በበላይነት የሚከታተሉ የትምህርት ቤት መሻሻል ምክትል ርዕሰ መምህራንና የክበብ ተጠሪ መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል ::

0 Comments