የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪ ወላጆች ማህበር (ተወማህ) የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲጎለብት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

by | ዜና

(ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም) ማህበሩ የ2017 ዓ.ም የአንደኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸሙን የከተማው የተማሪ ወላጆች ማህበር(ተወማህ) ምክር ቤት አባላት በተገኙበት ገምግሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻልና ግብአት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቀጸላ ፍቅረማርያም በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው የተማሪዎች ውጤትና ስነምግባር እንዲሻሻል የሚያከናውናቸው ተግባራት የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ በየደረጃው የሚገኙ የተማሪ ወላጅ ማህበር አደረጃጀቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው የምክር ቤት አባላቱ በውይይታቸው እስካሁን ያከናወኑትንም ሆነ በቀጣይ ሊተገበሩ በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ በመወያየት በቀጣይ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተማሪ ወላጆች ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ሀሰን ሽፋ በበኩላቸው ማህበሩ ከመጋቢት 26/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከትምህርት ቤት እስከ ከተማ ድረስ በአዲስ መልክ ተዋቅሮ ወደስራ መግባቱን ገልጸው ማህበሩ ወላጆችን በማስተባበር ለትምህርት ልማት ስራው ውጤታማነት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ሰብ ሳቢው አያይዘውም ማህበሩ በየትምህርት ተቋማቱ አከባቢ የሚገኙ አዋኪ ጉዳዮች እንዲወገዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ የክፍል ተማሪ ህብረት አባላትን በማስተባበር ለትምህርት ተቋማት የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

0 Comments