የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኢሬቻ በአልን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሄደ።

by | ዜና


(መስከረም 23/2017 ዓ.ም) የፓናል ውይይቱ “ኢሬቻ ለባህላችን ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል በሽማግሌዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ አጠቃላይ ሰራተኞችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የኢሬቻ በአል ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚያከብሩት በአል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘንድሮው በአል እሴቶቹን ጠብቆ እንዲከበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በመግለጽ የዛሬው ፓናል ውይይት ከኢሬቻ በአል አከባበር ጋርም ሆነ ከገዳ ስርአት ጋር በተገናኘ በቂ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ በበኩላቸው የኢሬቻ በአል አንድነትን እና ወንድማማችነትን የሚያጠናክር በአል እንደመሆኑ የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ በአል እሴቱን ጠብቆ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የቢሮው ሰራተኞች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪው ዶክተር ቁልቁሉ ስለ ኢሬቻ በአል አከባበር እና የገዳ ስርአትን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።

0 Comments