የትምህርት ቤት መሻሻልና ፕሮግራም ትግበራ ዳይሬክቶሬት ለተማሪ ወላጅ ማህበር(ተወማ) ተወካዮች ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ።

by | ዜና

(የካቲት 1/2017 ዓ.ም) የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን ቢሮው ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር በጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ የተማሪ ወላጅ ማህበር ተወካዮች መስጠቱን የቢሮው የትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያው አቶ ሳሙኤል አየለ ጠቁመው ስልጠናውም የልዩ ፍላጎት እና የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እንዲሻሻል እንዲሁም ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የወላጆች ኃላፊነት ምን መሆን እንዳለበትና ተዛማጅ ጉዳዮችን መሰረት አድርጎ መሰጠቱን አስታውቀዋል።

መማር ማስተማር ስራው የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት የሚችለው ወላጆች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ሲችሉ እንደመሆኑ ቢሮው በየደረጃው ከሚገኙ የተማሪ ወላጅ ማህበር አደረጃጀቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ የትምህርት ቤት መሻሻልና ፕሮግራም ትግበራ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ሙሉነህ ተክለብርሀን ገልጸው በዛሬው ስልጠና ተሳታፊ የሆኑ የተማሪ ወላጅ ተወካዮችም የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ወላጆች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በየአከባቢያቸው ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።


በኢፌድሪ ህገመንግስትም ሆነ በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ሁሉም ዜጎች ያለምንም ልዩነት የትምህርት  አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባቸው መደንገጉን የትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያ አቶ  አራጋው ዘውዴ ልዩ ፍላጎት ያለባቸው ህጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ የተማሪ ወላጅ ኮሚቴ አባላት ሚናን  በተመለከተ ስልጠና በሰጡበት ወቅት አስገንዝበዋል።

በመርሀ ግብሩ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል የወላጆች ሚና በሚል እና የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎን በተመለከተ የትምህርት ቤት መሻሻል ባለሙያ በሆኑት በአቶ ሱሪ ሹሜ እና በአቶ ሲሳይ ግርማ አማካይነት ስልጠና ተሰቷል።

0 Comments