በክቡር ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ የተመራ ቡድን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሚገኙት በአጼ ቴዎድሮስ ፣ በተባበሩት መምህራን ፣ በእውቀት ምንጭ እንዲሁም በመሰረተ ኢትዮጵያ ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የመስክ ምልከታ አካሄዳል፡፡

by | ዜና

(ጥር 29/2017 ዓ.ም) በመስክ ምልከታው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱን ጨምሮ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አዲሱ ሻንቆ(ዶክተር) ፣ የቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ የክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰማኸኝ አስታጥቄ እና ሌሎች የክፍለ ከተማና ወረዳ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

     

የመስክ ምልከታው በክፍለ ከተማው በሚገኙት አጼ ቴዎድሮስ ፣ የተባበሩት መምህራን ፣ እውቀት ምንጭ እንዲሁም መሰረተ ኢትዮጵያ ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተካሄደ ሲሆን በጉብኝቱ በተቋማቱ እየተገነቡ የሚገኙ የመማሪያ ህንጻዎች ፣ የመመገቢያ አዳራሽ እንዲሁም አጠቃላይ ምድረ ግቢያቸውን ጨምሮ የቤተ ሙከራዎችን ፣ የአይ ሲቲ ማዕከላትን እና የቤተ መጽሀፍ ክፍሎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

         

በአጼ ቴዎድሮስ እና በዕውቀት ምንጭ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ህንጻዎች የቤተ ሙከራን ጨምሮ አንዳንድ የተጓደሉ ቁሳቁሶችን በማሙዋላት ለመማር ማስተማር ስራው ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለሚመለከታቸው አካላት አቅጣጫ ሰጥተዋል።

       

በተመሳሳይ በተባበሩት መምህራን እና መሰረተ ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በመገንባት ላይ የሚገኙ ህንጻዎች ጥራታቸው ተጠብቆ በፍጥነት እንዲጠናቀቁና ሞዴል ሆነው ለተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ግንባታውን ለሚያካሂዱ ኮንትራክተሮችና ክትትል በማድረግ ላይ ለሚገኙ አመራሮች ዶክተር ዘላለም የስራ መመሪያ አስቀምጠዋል።

0 Comments