(ጥር 19/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በትምህርት ቤቶች እየተከናወኑ ያሉ የከተማ ግብርና ስራዎችን ግምገማ ለሚያካሂዱ ባለሙያዎች መመዘኛ መስፈርቱን አስመልክቶ ገለጻ ሰጥቷል::
በ11ዱ ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 151 ትምህርት ቤቶች በግምገማ ሂደቱ እንደሚያልፉ የገለፁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ወንድሙ ኡመር ግምገማው ቀጣይ በትምህርት ቤቶች እየተሰራ ያሉ የከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች የታለመላቸውን አላማ እንዲያሳኩ ቢሮው የድጋፍና ክትትል ስራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አቅም ይፈጥራል ብለዋል :: አክለውም በምዘና ሂደቱ የከተማ ግብርና ላይ የማይሰሩ ትምህርት ቤቶችን ለማወቅና ያጋጠማቸውን ክፍተት በመለየት ለቀጣይ መደላድል ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው ምዘናው በመንግስት ትምህርት ቤቶች ያሉ የከተማ ግብርና ሥራዎች ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በመመልከት በስራው ላይ ያለውን አፈፃፀም በአግባቡ እየተገበሩ ላሉ ትምህርት ቤቶች በተሻለ መነቃቃት ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እውቅና ለመስጠትና እንዲሁም ለሌሎች የልምድ ልውውጥ ማዕከል እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል:: ምክትል ቢሮ ኃላፊው በተጨማሪም በቀጣይ በሚገኘው የምዘና ውጤት መሰረትም ዝቅ ያለ አፈፃፀም ያላቸው ትምህርት ቤቶች በሁለተኛ መንፈቀ ዓመት ራሳቸውን ለተሻለ ሥራ እንዲያዘጋጁ አቅም የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል::
0 Comments