በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በፋይናንስ ፤ በግዢና በኦዲት ዳይሬክቶሬቶች በጥምረት የተዘጋጀ ስልጠና መሰጠት ጀመረ፡፡

by | ዜና

(ጥር 2/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፋይናንስ ፤ ግዢና ኦዲት ዳይሬክቶሬቶች በፋይናንስ አሰራርና መመሪያ ፤ በግዢ ጽንሰ ሃሳብና መመሪያ እንዲሁም በውስጥ ኦዲት ቁጥጥር አሰራር ላይ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ አሳውቀዋል፡፡

               

በስልጠናው መክፈቻ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ በፋይናንስና ግዢ ጉዳዮች ላይ ለባለሙያዎች ስልጠና መስጠት አሰራርን ባለመጠበቅ የሚመጣን ተጠያቂነት ለማስቀረት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡ አቶ ሲሳይ እንዳሉት ስልጠናው አሰራርን ባለመጠበቅ የሚመጣን ተጠያቂነት ከማስቀረት ባለፈ ቀደም ሲል የሚያውቁትን እውቀት በማስታወስ የህዝብና የመንግስትን ሃብትን ለታለመለት አላማ ለማዋል እንዲሁም ስራን በአግባቡ ለማከናወን አቅም እንደሚፈጥር አብራርተዋል፡፡ ሰልጣኞችም የስልጠናውን ጠቀሜታ በመረዳት በንቁ ተሳታፊነት ስልጠናውን እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ መክብብ በለጠ በቢሮውና በአዳሪ ትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ባሉ የስራ ክፍሎች ላሉ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱ መልካም መሆኑን ጠቅሰው ሰልጣኞች በተግባር ሂደት ያጋጠማቸውን ችግሮች እያነሱ የሚማማሩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ቀደም ሲል ያውቁት የነበረውን አሰራር ለማስታወስ አቅም ይፈጥርላቸዋል ብለዋል፡፡

የቢሮው የግዢ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ ረብሶ በበኩላቸው በግዢ መመሪያና ጨረታ ሰነድ አዘገጃጀትና የውል አስተዳደር ጽንሰ ሃሳብና መመሪያ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በሚኖረው ስልጠና የፋይናንስ መመሪያና ደንቦች ብሎም የጥሬ ገንዘብ አስተዳደር ስርዓትን ለማሳወቅ እንዲሁም በውስጥ ኦዲት ቁጥጥር ስራዎች ላይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ቀሪ የስልጠና ሰነዶች ቀርበው በስልጠናው ተሳታፊዎች ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በስልጠናው የቢሮው ባለሙያዎችን ጨምሮ ፤ የገላን ወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ፤ የብርሃን አይነስውራን እና እቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

0 Comments