በ6ወራት የተከናወኑ ጠንካራ አፈጻጸሞችን በማስቀጠልም ሆነ በሂደት የተስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባ ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ሳምሶን መለሰ ገለጹ።

by | ዜና

(ታህሳስ 19/2017 ዓ.ም) ምክትል ቢሮ ኃላፊው በሚያስተባብሩት ዘርፍ የሚገኙ ስራ ክፍሎችን ማለትም የቢሮው የትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ፣ የትምህርት ቴክኖሎጂ ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት እንዲሁም የግብአት እቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት የ6 ወር እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግመዋል።

በውይይቱ በሶስቱ ዳይሬክቶሬቶች ስር የሚገኙ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ የዘርፉ ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የዳይሬክቶሬቶቹ የ2017 ዓ.ም 6ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የዘርፉ አስተባባሪ አቶ ሳምሶን መለሰ በስድስቱ ወራት በሶስቱ ዳይሬክቶሬቶች በርካታ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው በተለይም ጥራቱን የጠበቀ መረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፈ መረጃ ጥራቱን ጠብቆ ለተገልጋዩ ተደራሽ እንዲሆን መረጃዎችን የማጥራት ስራውን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ሀላፊው አክለዉም የትምህርት ግብዓት ስርጭት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀፍቱ ብርሀኑ በስድስቱ ወራት በስራ ክፍሉ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ጥራቱን የጠበቀና ተአማኒነቱ የተረጋገጠ መረጃ በማደራጀትና በማጥራት ለተገልጋዩ ተደራሽ ከመደረጉ ባሻገር ከተለያዩ ስራ ክፍሎች ጋር የውስጥ ትስስር በመፍጠር ውጤታማ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማትና ማስፋፋት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ዳኜ በበኩላቸው በበጀት አመቱ ስድስት ወራት በኢ-ስኩል ሲስተም አማካይነት የተማሪዎች ምዝገባ እንዲካሄድ እንዲሁም የመምህራን እና የተማሪዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የትምህርት መረጃዎች በሲስተሙ አማካይነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ስራ ክፍሉ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣቱን ገልጸዋል።

0 Comments