(የካቲት 13/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በከተማ አስተዳደሩ በበይነ መረብ ኦን ላይን ለመስጠት በሚያስችል እቅድ ላይ ከክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤት አስተባባሪዎችና ቡድን መሪዎች ጋር ውይይት አካሂዳል፡፡
በውይይቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ማስፋፋት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ዳኜ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ የተዘጋጀን እቅድ አቅርበው ውይይት ተካሄዳል::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ መድረኩ ቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለሚደረግ ውይይት ሰፊ ግብአት የሚገኝበት መሆኑን ጠቁመው በ2016 ዓ.ም ፈተና አሰጣጥ የነበሩ ችግሮችን በመለየት ከችግሩ መውጫ ለማመቻቸት ቀደም ብሎ በእቅድ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በየትምህርት ቤቱ ያሉ የአይቲ ባለሙያዎችንና ግብአቶችን በአግባቡ መጠቀም ለፈተናው ስኬት የራሱ ሚና እንዳለው በመረዳት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል::
የቢሮው ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ በበኩላቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ለፈተናው ዋና ባለቤት መሆናችሁን በመረዳት መረጃን በማጥራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ራስን ማዘጋጀት ይገባችኅል ብለዋል:: አክለውም ከዚህ በፊት በተሰጠ ፈተና የነበሩ ችግሮችን በመለየት በእቅድ መመራት ለፈተናው ስኬት የራሱ በጎ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው በመረዳት ከባለሙያ ጀምሮ በትኩረት መስራት ይጠበቃል ብለዋል::
በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አማካሪ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ ፣ የቢሮው ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ ፣ የቢሮው አማካሪ አቶ ጥላሁን ፈቃዱ ፣ የክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤት አስተባባሪዎች፣ ቡድን መሪዎችና የቢሮ ባለሙያዎች ተገኝተዋል::
0 Comments