የ2017 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የቀጥታ (ኦንላይን) ምዝገባን አስመልክቶ ስልጠና ተሰጠ ፡፡

by | ዜና

(ታህሳስ 4/2017 ዓ.ም) ስልጠናው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አማካይነት በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለሚያስፈትኑ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ነው የተሰጠው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ቀደም ሲል ተመሳሳይ ስልጠና ለክፍለከተማ የፈተና አስተባባሪዎችን ጨምሮ ለፈተና እና አይ ሲቲ ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልጸው በዛሬው ስልጠና የአስፈታኝ ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን ተፈታኝ ተማሪዎችን በ2016 ዓ.ም በነበረ የኦንላይን ምዝገባ ያጋጠሙ ችግሮችን በዚህ አመት ተቀርፈው ተማሪዎችን ከወዲሁ በአግባቡ ኦን ላይን በመመዝገብ ለፈተናው ዝግጁ ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

የቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ባለሙያው አቶ እንደሻው መልሴ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት የ2017 ዓ.ም ሃገር አቀፍ የኦንላይን ምዝገባን በአግባቡ ለማካሄድ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ምዝገባ ሂደት መገምገሙን ጠቁመው በ2017ዓ.ም በተሻለና በተቀመጠው የድርጊት መርሀ ግብረ መሰረት ምዝገባው እንዲካሄድ የርዕሳነ መምህራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ለሚሰጠው የ2017 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የተፈታኞች ኦንላይን ምዝገባ ከታህሳስ 7 እስከ ጥር 6/ 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከስራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

0 Comments