(ቀን 2/04/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለሚወስዱ ተፈታኞች የኦንላይን ምዝገባ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ በ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሃገር አቀፍ ፈተና የኦንላይን ምዝገባ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ስልጠናው በዚህ ጊዜ መሰጠቱ በምዝገባ ሂደት የሚያጋጥሙ የስም ፊደል ስህተት ፤ የፎቶግራፍ ጥራትና ችግሮች እንዳያጋጥሙ የፈተና ባለሙያዎች ከአይሲቲ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ጥራትና ወቅቱን የጠበቀ ምዝገባ እንዲካሂዱ አቅም ይፈጥራል ተብሏል ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዲነዖል ጫላ በስልጠናው ላይ በመገኘት ለሰልጣኞች ባስተላለፉት መልእክት በ2016 ዓ.ም በተደረገ የኦንላይን ምዝገባ ስርዓት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለዚህ አመት ምዝገባ እንደትምህርት በመውሰድ ምዝገባውን በጥራት ለማከናወን እንዲቻል ሰልጣኝ ባለሙያዎች ራሳቸውን ብቁ እንዲያደርጉና እንዲሁም ታች ድረስ በመውረድ ለመዝጋቢዎች ለሚሰጡት ስልጠና ራሳቸውን ዝግጁ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አያይዘውም ስልጣኞች ተማሪዎች የሚጠብቁት ውጤት ላይ መድረስ እንዲችሉ ምዝገባው የተቀመጠለትን የጊዜ ገደብና ጥራት በጠበቀ መልኩ እንዲከወን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ላይ በትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡
የፈተና ዝግጅት አስተዳደር ባለሙያ የሆኑት አቶ እንደሻው መልሴ ስልጠናውን በሰጡበት ወቅት እንዳሉት የ2017 ዓ.ም ሃገር አቀፍ የኦንላይን ምዝገባን ለማካሄድ በ2016 ዓ.ም በምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ እጥረቶችን በመለየት የአፈጻጸም ግምገማ መካሄዱን ጠቁመው ቀድሞ ከነበረው እጥረት በመማር በቂ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል፤ አክለውም የፈተና ባለሙያዎች ምዝገባውን በበላይነት የሚመሩ በመሆኑ ስልጠናውን በትኩረት እንዲከታተሉና በቀጣይ በትምህርት ቤት ለሚገኙ የምዝገባ ባለሙያዎች ስልጠናውን በማስተላለፍ የምዝገባውን ትግበራ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል ፡፡
በስልጠናው በሁሉም ክፍለከተሞች የሚገኙ የፈተናና አይሲቲ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠው የ2017 ዓ.ም 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ተፈታኞች ኦንላይ ምዝገባ ከታህሳስ 7 እስከ ጥር 6/ 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከስራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
0 Comments