(ጥር 26/2017 ዓ.ም) በስልጠናው በሁሉም የመንግስት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንን ጨምሮ የአንደኛ ደረጃ ርዕሳነ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን ስልጠናውን በጫወታ በማስተማር ስነ ዘዴ የማሰልጠን ልምድ ያላቸውና የአስልጣኞች ስልጠና የወሰዱ ባለሙያዎች በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ከስራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው ስልጠናው ከዚህ በፊት በጫወታ የማስተማር ስነ ዘዴ ዙሪያ ስልጠና ላልወሰዱ በአማርኛ እና አፋን ኦሮሞ ስርአተ ትምህርት ለሚያስተምሩ የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራን እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩዋ አያይዘውም የቅድመ አንደኛ ደረጃ መምህራኑ በጫወታ የማስተማር ስነ ዘዴውን በአግባቡ ተግባራዊ አድርገው ለህጻናቱ በቂ ዕውቀት እንዲያስጨብጡና ርዕሳነ መምህራኑም ሆኑ ሱፐርቫይዘሮቹ ደግሞ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን አመላክተዋል።
በመርሀ ግብሩ በጫወታ ከማስተማር ስነ ዘዴ ባሻገር በመርጃ መሳሪያ አዘገጃጀትና ከኮርነር አደረጃጀት ጋር በተገናኘም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ወይዘሮ በላይነሽ ገልጸው ቢሮው በቀጣይ በየትምህርት ቤቱ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
0 Comments