(ህዳር 28/2017 ዓ.ም) ረቂቅ ሞጁሎቹ በአመታዊ የትምህርት መረጃ መጽሄት (Educational statstics Annual abstract manual) አዘገጃጀት እና የትምህርት አመላካቾችን (Educational indicators) ጋር በተገናኘ የተዘጋጁ ሲሆን በግምገማው የቢሮው የመረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ባለሙያዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ የዘርፉ ቡድን መሪዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የቢሮ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሀፍቱ ብርሀኔ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ዘመኑ ጥራቱን የጠበቀና ተአማኒነት ያለው መረጃ የሚፈለግበት እንደመሆኑ በትምህርት ሴክተሩ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ጥራታቸው በተጠበቀ ሁኔታ ተደራጅተው ለውሳኔ ሰጪ አካላትም ሆነ ለሌሎች አገልግሎት ፈላጊዎች በአግባቡ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመው በዛሬው መርሀ ግብር ሁለቱን ረቂቅ ሞጁሎች በመገምገም የሚሰጡ የማስተካከያ ሀሳቦችን በማካተት ለቢሮው ማኔጅመንት አባላት ቀርበው ሞጁሎቹን ወደ ተግባር የማስገባት ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ደስታ አብረሀም በበኩላቸው አመታዊ የትምህርት መረጃ መጽሄት የትምህርት አመላካቾችን መሰረት አድርጎ የሚዘጋጅ በመሆኑ አመታዊ መጽሄቱ በምን መልኩ መዘጋጀት እንደሚገባው እና የትምህርት አመላካቾቹ በመጽሄቱ እንዴት መካተት እንደሚገባቸው በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ ሞጁሎቹን ማዘጋጀት ማስፈለጉን አስታውቀዋል።
በመርሀግብሩ ሞጁሎቹን ከመገምገም ባሻገር ክፍለ ከተሞች የሰበሰቡትን መረጃ መሰረት አድርገው የ2016 ዓ.ም አመታዊ የትምህርት መረጃ መጽሄት ማዘጋጀት እንዲችሉ በጋራ እና በቡድን በመሆን መረጃዎችን የመተንተን ስራ መስራታቸውን የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ አዲስ ዘገየ ገልጸዋል።
የመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች ሁለቱን ረቂቅ ማኑዋሎች ከመገምገማቸው ባሻገር የ2016ዓ.ም ዓመታዊ የትምህርት መረጃ መጽሄት ለማዘጋጀት የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመተንተን የተለያዩ የማስተካከያ ነጥቦችን አስቀምጠዋል።
0 Comments