የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመምህራን ስልጠና መስጠት ጀመረ ::

by | ዜና

(ጥቅምት 23/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር  ለስራና ተግባር ትምህርት (CTE) መምህራን ለሶስት ሳምንታት የሚቆይ ስልጠና መስጠት ጀምሯል ::

ስልጠናው የስራና ተግባር ትምህርት (CTE) መምህራን በት/ት ቤቶች ሊተገብሯቸው ስለሚገቡ የማስተማር ስነ-ዘዴ እና ስትራቴጂዎች ፣ የምዘና ስርአት ፣ የክፍል ውስጥ መማር ማስተማር ሂደት አስተዳደር እና የመምህር ተማሪ ተግባቦት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ በመሰጠት ላይ መሆኑ ተገልፅዋል ::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ  ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ከምክትል ቢሮ ኃላፊ ከአቶ አሊ ከማል ጋር ተገኝተው ስልጠናውን ባስጀመሩበት ወቅት ለስልጠናው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት  ብቁ ተማሪ በማፍራት ሂደት ውስጥ የመምህራን ሚና ትልቁን ድርሻ  እንደሚይዝ ተናግረው መምህራን ለተማሪዎች ተገቢውን እውቀት በተገቢ የማስተማር ዘዴ ለማስተላፍ እንዲችሉ  በስልጠና መደገፍ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ሰልጣኞችም በጥብቅ ዲሲፕሊን ስልጠናውን በመከታተል ከስልጠናው ያገኙትን ክህሎትና እውቀት በመጠቀም ለተማሪዎቻቸው በሚሰጡት የሙያ ዘርፍ ትምህርቶች ላይ ውጤታማነትን ማረጋገጥና በንድፈ ሀሳብ ያገኟቸውን እውቀተቶች እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንደሚችሉ በማለመማድና በማብቃት ብቁ ዜጋ የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል ::

የመምህራን ትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ አድማሱ በበኩላቸው መምህራን በመደበኛ ከሰለጠኑበት ሙያ ጎንለጎን በመማር ማስተማር ሂደት ሊያዳብሩ የሚገባቸውን ክህሎት ለማሻሻል ተመሳሳይ ስልጠናዎች መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል ::

በአጠቃላይ ትምህርት ስርአታችን ውስጥ ተገቢ ትኩረት ተነፍጎት የነበረው የሙያ(ስራና ተግባር) ትምህርት አሁን በተደረገው የትምህርት እና ስልጠና ፖሊሲ ማሻሻያ  ምላሽ ማግኘቱን ጠቁመው የሥራና ተግባር ትምህርት አፈፃፀምን በማሳደግ እውን ለማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ከመምህሩ እንደሚጠበቅ አብራርተዋል ::

ስልጠናው በኮተቤ ትምህርት ዩንቨርስቲ መምህራን 536 ለሚሆኑ የ 11ኛ ክፍል መምህራን እየተሰጠ እንደሆነ ከዳይሬክቶሬቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል ::

0 Comments