የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ግዢ ዳይሬክቶሬት በመንግስት ግዢ አዋጅና መመሪያዎች ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡

by | ዜና

(ጥር 27/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ግዢ ዳይሬክቶሬት በመንግስት ግዢ አዋጅና መመሪያዎች ላይ ለሚመለከታቸው አካላትን በማሳተፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ በስልጠናው መክፈቻ ላይ በመገኘት ለስልጣኞች ባስተላለፉት መልእክት ስልጠናው ቢሮው ሥራዎችን ለማስፈፀም የሚያደርጋቸው ግዢዎች መመሪያና ደንቦችን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወኑና በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመቀነስ የሚረዳ መሆኑን አብራርተው ፤ ሰልጣኞችም ወቅቱ ከሚጠይቀው እውቀት አንጻር ብቁ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል፡፡

ጽ/ቤት ሃላፊው አክለውም ሰልጣኞች የስልጠናውን ርዕሰ ጉዳይ በተለያየ መንገድ የሚያውቁት ቢሆንም በስራቸው ላይ ያላቸውን እውቀት እርስበርስ እንዲያዳብሩ የውይይት መነሻ ከመሆን ባለፈ ለብልሹ አሰራር የመጋለጥ እድልን የመቀነስ ሚናው ጉልህ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የቢሮው ግዢ ዳይሬክቶሬት ዳይክተር ወ/ሮ አልማዝ ረብሶ በበኩላቸው የመንግስትን ግዢ በህግና መመሪያ መፈጸም እንዲቻል ወቅቱን የጠበቁ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች መስጠት በስራው ላይ የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለማረም የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፤ ሰልጣኞች ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል በሚያገኙት ግንዛቤ መሰረት በብቃት ስራን የማከናወን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ስልጠናው ከአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ በመጡ የግዢ ስልጠና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ በሆነቡት አቶ ደሴ አዳም በመንግስት ግዢ አፈፃፀም አጠቃላይ ገጽታና ምንነት ፤ የግዢ አፈጻጸም የህግ ማእቀፎች እንዲሁም የመንግስት ግዢ አላማና መርሆዎች ላይ ትኩረት በማድረግ እየተሰጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በስልጠናው የቢሮው እንዲሁም የገላን ወንዶች አዳሪና እቴጌ መነን የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግዢ ፤ ፋይናንስ፤ ኦዲትና ንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Comments