(ታህሳስ 8/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በአጠቃላይ የሥራ አፈፃፀምና እና የሪፎርም ስራዎች የተሻለ ውጤት ያመጡ ዳይሬክቶሬቶች በቢሮው ለሚገኙ ሌሎች ዳይሬክቶሬቶችና ቡድን መሪዎች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡
ልምድ ልውውጡ በዋናነት ልምድ የሚያካፍሉት ዳይሬክቶሬቶች የተሰጠን ተግባር በምን መልኩ እንዳከናወኑና በላቀ አፈጻጸም ለማከናወን የተጠቀሟቸውን ዘዴዎችና የዶክመንት አደረጃጀታቸው ላይ ትኩረት ያደረገ ግንዛቤ ለልምድ ልውውጡ ተካፋዮች አቅርበዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና በትምህርት ስራ አፈጻጸም የረካ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተሻለ የስራ አፈጻጸም ያላቸውና የደንበኞችን ጥያቄ በአግባቡ የሚመልሱ የስራ ክፍሎችን ማደራጀት የተቋም ዋና ኃላፊነት መሆኑን የተናገሩት የቢሮ ኃላፊ አማካሪና የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍ ምዘና ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ መደበኛ ተግባራትን ለማከናወንና የሪፎርም ስራዎችን አፈጻጸም ለማሳደግ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ዳይሬክቶሬቶች የሚያሳዩትን ጥንካሬ ዝቅተኛና መካከለኛ አፈጻጸም ላላቸው ስራ ክፍሎች ልምድ በማካፈል ከቀደመው ጊዜ የተሻለ የእቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት እንዲሁም ሰነዶችን የመሰነድ ዘዴዎችን ብሎም የአሰራር ዘዴዎችን ግልጽ በማድረግ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሃላፊዋ አክለውም ቢሮው በከተማ ደረጃ በተሻለ ስራ አፈጻጸም እውቅና ሲሰጠው የቆየ መሆኑን አንስተው የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች አሳታፊ እውቀት በመገብየት ራስን ለተሻለ ስራ በማዘጋጀት ወደ ተቀራራቢ አፈጻጸም እንዲመጡና የስራ ተነሳሽነታቸውን እንዲያሳድጉ አሳስበዋል፡፡
የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍ ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋአገኘሁ ለገሰ ቀደም ሲል ከከተማ እስከታች በተደረገ ክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ መሰረት ፍረጃ የተደረገ መሆኑን አብራርተው በፍረጃው መሰረት ዝቅተኛና መካከለኛ ውጤት ያስመዘገቡ ዳይሬክቶሬቶች ወደከፍተኛ ለማምጣት የውስጥ ልምድ ልውውጥ ማድረግ እንዳስፈለገ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም በክፍለከተሞች በመገኘት ልምድ ልውውጥ ለማካሄድ እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
በልምድ ልውውጡ ላይ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ወ/ሮ በላይነሽ የሻው እና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አበበ ቸርነት የእቅድና ሪፖርት አዘገጃጀት ፤ የሰነዶችን የመሰነድ ዘዴዎችና ሌሎች የአሰራር ሂደቶችን የያዘ ሰነዶች በማቅረብ ልምዳቸውን ሌሎች የቢሮው ዳይሬክቶሬቶች ያካፈሉ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሁለቱም ቢሮዎች በመገኘት የሰነዶችን አደረጃጀት ምልከታም ተካሄዳል፡፡
0 Comments