(ጥር 29/2017 ዓ.ም) በሁሉም ክፍለ ከተማ የሚገኙ የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ሰብሳቢና ሥራ አስፈፃሚ አባላት ከለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ መምህራን ማህበር ጋር የልምድ ልውውጥ አካሂደዋል ::
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በልምድ ልውውጡ ላይ በመገኘት ለልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች ባስተላለፉት መልእክት የትምህርት ሥራ የሁሉንም አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም የመምህሩ ድርሻ ደግሞ ላቅ ያለ መሆኑን በመረዳት መምህራን ማህበሩ ለትምህርት ሥራ ቁልፍ የሆነውን መምህር አቅም በማጎልበትና የመምህሩን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር እየሰራ ያለውን ሥራ አድንቀዋል::
አቶ አሊ አክለውም ማህበሩ የትምህርት ስራን ለመደገፍ በርካታ ሥራዎች እያከናወነ ቢሆንም ያልተሰሩ ተግባራት ለማከናወንና ወደ ተቀራራቢ አፈፃፀም ለመምጣት ልምድ ልውውጥ ማካሄድ የራሱ በጎ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተናግረዋል:: የልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎችም የወሰዱትን ልምድ ወደራሳቸው ቀይረው ብቁ ዜጋ የማፍራት ጥረቱን እንዲደግፉና የማህበሩን አቅም እንዲያሳድጉ ይጠበቃል ብለዋል::
የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ በበኩላቸው መምህራን ማህበሩ የትምህርት ጥራት ለማምጣትና የመምህራንን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር በርካታ ሥራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመው የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ክፍለ ከተሞች ልምዳቸውን ለሌሎች በማካፈል ሥራችን ግብ እንዲመታና ለትምህርት ጥራት ማህበሩ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ አቅም ይፈጥራሉ ብለዋል:: ተሳታፊዎችም የልምድ ልውውጡ የተነሱ ነጥቦችን ወደራሳቸው በመቀየር ተግባር ላይ እንዲያውሉት አሳስበዋል ::
የመምህራን ማህበር የመምህራንን ጥቅም ለማስከበር ጎንለጎን መምህራንና የትምህርት ማህበረሰቡ ላቅ ወዳለ ማህበረሰብ አቀፍ ሥራ የማስገባት አላማው መሆኑን የተናገሩት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አበበ በልምድ ልውውጡ የተነሱ ነጥቦች ማህበሩን ጠንካራ ተቋም እንዲሆን የሚያግዝ መሆኑንና እጅ ለእጅ ተያይዞ አላማን ማሳካት እንደሚገባ አብራርተዋል ::
በልምድ ልውውጡ ላይ የለሚኩራ ክፍለ ከተማ መምህራን ማህበር ሰብሳቢ መምህር ሚኪያስ ምንዳ ለሌሎች ልምድ የሚሆኑ የአሰራርና የመረጃ አያያዝ ስርዓቶችን የያዘ ሰነድ አቅርበው በልምድ ልውውጡ ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል::
0 Comments