(ጥቅምት 9/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻል ፕሮግራም ትግበራ ዳይሬክቶሬት የትምህርት ቤት መሻሻል ቡድን የሴትና የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ትምህርት ድጋፍን በሚመለከት ለወላጆች ስልጠና በመስጠት ላይ መሆኑን አሳውቋል::
ስልጠናው የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ሂደት የወላጆች ሚና ፣ ለአካል ጉዳተኛ የሚደረግ ድጋፍና እንክብካቤ ፣ የሴት ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎ እንዲሁም የትምህርት መሻሻል ፅንሰ ሃሳብ ላይ ትኩረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ በተማሪ ወላጆች ውይይት የሚደረግበት መሆኑ ተገልፅዋል ::
የትምህርት ቤት መሻሻልና ግብዓት አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቀጸላ ፍቅረማርያም ስልጠናውን ባስጀመሩበት ጊዜ እንዳሉት በስልጠናው የሚቀርቡ ርዕሰ ጉዳዮች የተማሪዎችን ሁለንተናዊ እድገትና የትምህርት ውጤትን ለማሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግ አብራርተው ወላጆችም የተማሪን ውጤትና ባህሪ ለማሻሻል በተለይም ሴቶችና አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ለማብቃት ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል ::
ዳይሬክተሩ አክለውም የስልጠናው ተሳታፊ ወላጆች በክፍለ ከተማቸው የሚገኙ የአካል ጉዳት ያለባቸው እና ሴት ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡና ከመጡም በኃላ ብቁ እንዲሆኑ ከግብአት ማሟላትና ምቹ የመማሪያ ቦታን ከማዘጋጀት አንፃር ከቢሮውና ከተማሪ ወላጆች ምን ይጠበቃል የሚለው ላይ ግንዛቤ የሚወስዱበት ይሆናል ብለዋል ::
የልጆችን ውጤት ለማሻሻል የወላጆችን ሚና በተመለከተ ሰነድ ያቀረቡት አቶ ረቢራ ዱጋሳ በበኩላቸው የተማሪ ውጤታማነት ላይ ወላጆችና አሳዳጊዎች ባለድርሻ ሳይሆን ባለቤት መሆናቸውን በመገንዘብ የተማሪ ውጤት መሻሻል ላይ አዎንታዊ እንክብካቤና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል ::
ስልጠናው UNICEF ድጋፍ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ለመጡ የተማሪ ወላጆች በተጠቀሰው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለሶስት ቀናት የሚሰጥ ሲሆን ቀጣይ በሌሎች ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ወላጆች ተመሳሳይ ርዕስ ላይ የሚሰጥ መሆኑን ከዳይሬክቶሬቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል::
0 Comments