(ጥር 20/2017 ዓ.ም) የትምህርት መረጃዎቹ በቅጹ ላይ በተቀመጠው መጠይቅ መሰረት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች በመሞላት ላይ የሚገኙ ሲሆን የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ወልደኪዳን ከቡድን መሪዎቹ አቶ ደስታ አብረሀም እና ከአቶ አዲስ ዘገየ ጋር በመሆን በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች እና ክፍለከተማ ትምህርት ጽህፈትቤቶች ተገኝተው ምልከታ አካሂደዋል።
የአመታዊ የትምህርት መረጃ መሙያ ቅጹ በኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በቢሮው አማካይነት ወደ ትምህርት ቤቶች መላኩን የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ታዬ ወልደኪዳን ጠቁመው ተቋማቱ መረጃዎቹን በተላከው ቅጽ መሰረት በመሙላት ላይ እንደሚገኙ በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን አስገንዝበዋል።
መረጃዎቹ እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ ተሞልተው በትምህርት ሚኒስቴር ወደበለጸገው stat edu2.2017 ሶፍትዌር የማስገባት ስራ እንደሚሰራ የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ደስታ አብረሀም ገልጸዋል።
የትምህርት መረጃዎቹ ወጥ ሆኖ በተዘጋጀ ቅጽ ተሞልተው መደራጀታቸው ለአገልግሎት ፈላጊውም ሆነ ለፖሊሲ አውጪዎች ተአማኒነቱ የተረጋገጠና ጥራቱን የጠበቀ መረጃ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያስችል የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት መረጃ ዝግጅትና አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ አዲስ ዘገየ አስታውቀዋል።
0 Comments