ተማሪዎችን በሒሳብና እንግሊዘኛ የትምህርት አይነቶች ውጤታማ ለማድረግ የተዘጋጀው ስትራቴጂ አፈጻጸምን አስመልክቶ በተካሄደ የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(ጥቅምት 8/2017 ዓ.ም) ድጋፍና ክትትሉ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶችና በክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ በድጋፍና ክትትሉ የተሳተፉ ሱፐርቫይዘሮችን ጨምሮ ርዕሳነ መምህራን እና የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በመርሀ ግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ቢሮው በ2017 ዓ.ም የትምህርት አመት ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰባቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚማሩ ተማሪዎችን በሒሳብና እንግሊዘኛ የትምህርት አይነቶች ውጤታማ ማድረግ መሆኑን ጠቁመው ተማሪዎች በሁለቱ የትምህርት አይነቶች የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችል ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን አመላክተዋል።

ዶክተር ዘላለም አያይዘውም ቀደም ሲል ስትራቴጂው ለትምህርት ተቋማት መውረዱን በመጥቀስ በየትምህርት ተቋማቱ የስትራቴጂው አተገባበር ምንደረጃ ላይ እንደሚገኝ የድጋፍና ክትትል ስራ መሰራቱን ገልጸው በዛሬው ውይይትም በድጋፍና ክትትሉ ግብረመልስ ላይ በመወያየት በቀጣይ በተቋማቱ የተቀራረበ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ታስቦ መካሄዱን አስገንዝበዋል።

የቢሮው የአጠቃላይ ትምህርት ሱፐርቪዥን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱልበር መሀመድ የድጋፍና ክትትል ግብረመልሱን ያቀረቡ ሲሆን የውይይቱ ተሳታፊዎች በቀረበው ግብረ መልስ ዙሪያ የተለያዩ አስተያየቶችን እና ጥያቄዎችን አቅርበው በኃላፊዎች ምላሽና በቀጣይ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራትን የተመለከተ የስራ አቅጣጫ ተሰቷል።

0 Comments