(ጥር 8/2017 ዓ.ም) በመርሀ ግብሩ ከትምህርት ቢሮ ጋር ትስስር ፈጥረው የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ከሚገኙ ተቋማት የመጡ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና የቢሮው አጠቃላይ ካውንስል አባላት የተገኙ ሲሆን የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክተር አቶ ሀፍቱ ብርሀኑ በ6 ወሬት በቅንጅታዊ አሰራር እና በመልካም አስተዳደር የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሴቶች፣ወጣቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወይዘሮ ዘይነባ ሽኩር በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት በከተማ አስተዳደሩ በቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማ በመሆን ዕውቅና ማግኘት ከቻሉ ተቋማት መካከል አንዱ ትምህርት ቢሮ መሆኑን ገልጸው ቢሮው ዘንድሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ገላን ጉራ ቁ.2 ትምህርት ቤትን በ57 ቀናት ውስጥ ደረጃውን ጠብቆ ከቅድመ አንደኛ እስከ 2ኛ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረጉ በ6 ወር ውስጥ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የሚጠቀስ መሆኑን አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የትምህርት ስራ ትውልድ የሚገነባበትና የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ የሚፈጠርበት ሴክተር በመሆኑ ስራው የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የጋራና የተደመረ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ጠቁመው ቢሮው በቅንጅታዊ አሰራርም ሆነ በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላስመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማት ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ የትምህርት ጥራትን በማረገገጥ የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመማር ማስተማር አገልግሎቱ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችና በትምህርት ተቋማት አከባቢ የሚገኙ አዋኪ ተግባራት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ ችግሮቹ መቀረፋቸውን የቢሮ ኃላፊ አማካሪና የዘርፉ አስተባባሪ ወይዘሮ አበበች ነጋሽ አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ በቅንጅታዊ አሰራርና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ከቢሮው ጋር በመተሳሰር ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ተቋማት እና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ቢሮው ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ ላበረከቱት ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፣ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ እንዲሁም ለፕላን ልማት ቢሮ እና ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ዕውቅና ተሰጥቷል።
0 Comments