በ2017 ትምህርት ዘመን በ6ኛ ፣ 8ኛና 12ኛ ክፍሎች ኦንላይን ምዝገባ አፈጻጸም ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተካሄደ::

by | ዜና

(የካቲት 18/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ፈተናና ምዘና ዝግጅት አስተዳደር ዳይሬክቶሬ የ2017 ትምህርት ዘመን የ6ኛ ፣ 8ኛና 12ኛ ክፍሎች ኦንላይን ምዝገባ አፈጻጸም ያለበትን ደረጃን መሰረት በማድረግ ውይይት አካሄዳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ፈተናና ምዘና ዝግጅት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በለጠ ንጉሴ ክፍለ ከተሞች የምዝገባ ሂደቱን በዋናነት የሚመሩ እንደመሆናቸው የጋራ ውይይቱ ቀደም ሲል በተጠናቀቀዉ የኦንላይን ምዝገባ ሂደት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለማረምና ለቀጣይ ስራ ራስን ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡

የአጠቃላይ ፈተናና ምዘና ዝግጅት አስተዳደር የአማርኛ ቋንቋ ቡድን መሪ ወ/ሮ መሰረት ኩማ በበኩላቸው የ6ኛና 8ኛ ክፍል ምዝገባ በተቀመጠለት ቀነ ገደብ የተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው በውይይቱ የሚገኙ ግብአቶች በኦንላይን የተካሄደውን የምዝገባ ሂደት ለማጥራትና ያጋጠሙ ችግሮች ካሉ የ1 ሳምንት ተጨማሪ ጊዜ ለመስጠት እንደሚያስችል አብራርተዋል፡፡ በተጨማሪም በ12ኛ ክፍል ምዝገባ የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በማጥራት ወደ ሃገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ከመላካቸው በፊት መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የአጠቃላይ ፈተናና ምዘና ዝግጅት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ ደገፉ እንዲሁም ከተመረጡ ክፍለ ከተሞች የምዝገባ አካሄዱን አስመልክቶ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በውይይቱ የአጠቃላይ ፈተናና ምዘና ዝግጅት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪና ባለሙያዎች እንዲሁም የ11ዱ ክፍለ ከተሞች የአማርኛና አፋን ኦሮሞ ፈተና ዝግጅት ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

0 Comments