(ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ትምህርት ቢሮ እቅድ በጀት ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት እና የሪፎርምና አገልግሎት ክትትል ድጋፍ ምዘና ዳይሬክቶሬቶች በጋራ በመሆን በአገልግሎት አሰጣጥና ደንበኛ አያያዝ ምንነት እንዲሁም ስትራቴጂክ እቅድን ካስኬድ ማድረግና ሳይንሳዊ የምዝገባና የንጽጽር ስሌት አሰራር ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አማካሪና የዘርፉ ኃላፊ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ በዚህ በጀት ዓመት ለሶስት ጊዜ ክትትልና ድጋፍ ሥራዎች መከናወኑን ገልፀው በክትትልና ድጋፍ ስራው ውጤት መሰረት ፍረጃ በመስጠት በቢሮ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እንዲሁም ትምህርት ቤቶች የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ተቋማት ላይ በመገኘት ልምድ ልውውጥ ሲካሄዱ መቆየቱን የጠቀሱ ሲሆን በተጨማሪም በድጋፍና ክትትሉ የታዩ እጥረቶችን ለመሙላት ቢሮው የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እያካሄደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም ሰልጣኞች በስልጠናው ያዳበሩትን ክህሎት ታች ድረስ በማውረድ በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በስታንዳርድ አመዘጋገብና ካስኬዲንግ ላይ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና በትምህርት ተቋማቱ ተቀራራቢ አፈፃፀም እንዲኖሮ አቅም እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል ::
ቀደም ሲል በ456 ትምህርት ቤቶች 119 ወረዳዎችና በ11ክፍለ ከተሞች በተደረጉ ክትትልና ድጋፎች በእጥረት የታዩ ጉዳዮች አሁን በስልጠናው መዳሰስ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ቀጣይ አቅማቸውን ለማጎልበትና እጥረቶችን ለመቅረፍ የስራ ክፍሎቹ በተሻለ ትጋት እየሰሩ መሆኑን ሀላፊዋ ጨምረዉ ገልጸዋል::
ስልጠናው የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ አገልግሎት አሰጣጥና ስታንዳርዳይዜሽን አስተባባሪ በሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ይመር እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሃብት ልማት ቢሮ የአገልግሎት አሰጣጥ ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ በሆኑት አቶ እንዳልካቸው አማካኝነት በአገልግሎት አሰጣጥና ደንበኛ አያያዝ ምንነት ፣ እቅድን እስከታች ካስኬድ ማድረግ የሚያስችሉ ዘዴዎችና ሳይንሳዊ የምዝገባና የንጽጽር ስሌት አሰራር ላይ ትኩረት በማድረግ ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው የቢሮው ባለሙያዎች ፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ፤ የክፍለከተማ ቡድን መሪዎች እንዲሁም የክፍለ ከተማና ወረዳ ሱፐርቪዥን አስተባባሪዎች እየተሳተፉ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
0 Comments