(መስከረም 27/2017 ዓ.ም) በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ እና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ብርሀነ መስቀል ጠናን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮች፣ባለሙያዎች እንዲሁም ተሸላሚ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው የተገኙ ሲሆን ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ላፕቶፕና ታብሌቶችን ጨምሮ የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቱዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዕውቅና መርሀግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ውጤቱ በከፍተኛ ትጋትና ጥረት የተመዘገበ እንደመሆኑ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው እንዲሁም መምህራንን ጨምሮ በየደረጃው ለሚገኙ ባለድርሻ አካላት እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መንግስት ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የተማሪዎቻችን ውጤት መሻሻል እያሳየ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ክብርት ከንቲባዋ አክለውም የዛሬው የዕውቅና መርሀ ግብር በታችኛው የትምህርት እርከን ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ተነሳሽነት ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ሴክተሩ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በ2016 ዓ.ም 21.4% ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ማምጣታቸውን እና ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ5% እድገት መመዝገቡን ጠቁመው በዛሬው መርሀ ግብር ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች ባሻገር ተማሪዎቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ የትምህርት ተቋማት ዕውቅና እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።
በዕውቅና መርሀ ግብሩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበችው ተማሪ ሲፈኔ ተክሉን ጨምሮ ለሶስት ተማሪዎች የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል እንደሚሰጥ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ በ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና ወስደው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ተቋማት ዕውቅና ተሰጠ።
0 Comments