በትምህርት ተቋማት ለሚገነቡ አዳዲስ ህንጻዎች በተዘጋጁ ዲዛይኖች ላይ ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(የካቲት 20/2017 ዓ.ም) በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የህንጻዎቹ ግንባታ የሚካሄድባቸው ክፍለ ከተማ ትምህርት እና ዲዛይንና ግንባታ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የኮንስትራክሽን ስራው አማካሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

                

በመርሀ ግብሩ ግንባታዎቹ በሚካሄድባቸው በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በብሩህ ተስፋ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በመጋቢት 28 ትምህርት ቤት ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በኢትዮ ኮሪያ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በመሰረተ ኢትዮጵያ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንዲሁም በእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ እና በገላን የወንዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገነቡ G+4 ህንጻዎች ዲዛይን ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

                 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚገነቡ የG+2 ህንጻዎች ህጻናቱን በአካልና አዕምሮ በማበልጸግ ለቀጣዩ የትምህርት ደረጃ በአግባቡ ዝግጁ እንዲሆኑ በቂ የመጫወቻ ቦታዎችን እና ቁሳቁሶች እንዲዘጋጁላቸው በዲዛይኑ መቀመጡን ጠቁመው ግንባታውን የሚያካሂዱ ተቋራጮችም ሆኑ አማካሪዎች ግንባታው በዲዛይኑ በተቀመጠው መሰረት ለህጻናቱ ምቹና ሳቢ በሆነ መገንባት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ዶክተር ዘላለም አያይዘውም በእቴጌ መነን የልጃገረዶች አዳሪ እና በገላን የወንዶች አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገነቡት ሁለት የG+4 ህንጻዎች ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ የአይሲቲ ክፍሎችን ፣ የሳይንስ ትምህርት ቤተ ሙከራዎች እንዲሁም የመመገቢያ አዳራሾችን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ የጂም ክፍሎችን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ያካተተ ግንባታ እንደመሆኑ ቢሮው የህንጻዎቹን የግንባታ ሂደት በየተቋማቱ በመገኘት ክትትል የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።

0 Comments