(ህዳር 7/2017 ዓ.ም) ስልጠናው በየደረጃው ለሚገኙ የትምህርት ቤት መሻሻል ምክትል ርዕሳነ መምህራን ፣ለመምህራን፣ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተባባሪዎች እንዲሁም ለክፍለ ከተማ እና ወረዳ የትምህርት ቤት መሻሻል ቡድን መሪዎች እና ባለሙያዎች መሰጠቱን ከስልጠናው አዘጋጆች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻልና ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቀጸላ ፍቅረማርያም ስልጠናው በዋናነት ከትምህርት ቤት የዕውቅና ፍቃድ አሰጣጥ መርሀ ግብር ጋር በተገናኘ ለትምህርት ቤቶች ደረጃ ከመሰጠቱ በፊት ተቋማቱ ያሉበትን ሁኔታ በመገምገም ከወዲሁ በቂ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንዲችሉ ታስቦ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በትብብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ስልጠናው ትምህርት ቤቶች የዕውቅና ፍቃድ ከመውሰዳቸው በፊት ሊያሟሉ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ እንደመዘጋጀቱ የስልጠናው ተሳታፊዎች በየተቋሞቻቸው የሱፐርቪዥን ስራ እንደሚሰሩ ጠቁመው ቢሮው በቀጣይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የድጋፍና ክትትል ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
ስልጠናው በአስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች በተዘጋጁ 33 የስልጠና ጣቢያዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን እና በስሩ ከሚገኙ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በመጡ አሰልጣኞች መሰጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤት መሻሻልና ፕሮግራም ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ረቢራ ዱጋሳ አስታውቀዋል።
በትምህርት ቤት የዕውቅና ፍቃድ አሰጣጥ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።
0 Comments