በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተካሄደ የድጋፍና ክትትል ግብረ መልስ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(መስከረም 9/2017 ዓ.ም) በውይይቱ በ2016 ዓ.ም የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ተግባራዊ አድርገው ትራንስፎርም እንዲሆኑ የግብአት ድጋፍ ከተደረገላቸው 40 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በ2017 ዓ.ም ፕሮግራሙ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው 60 ተቋማት የተውጣጡ ርዕሳነ መምህራን እና አስተባባሪዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ የዘርፉ አስተባባሪዎች እና ቡድን መሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥም ሆነ የተማሪዎችን ስነምግባር ለማሻሻል መሰረት የሚጣልበት የትምህርት እርከን እንደመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ደረጃው በሰጠው ትኩረት ለተቋማቱ በከፍተኛ በጀት የግብአት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው በተቋማቱ በተካሄደ ምልከታ የተገኙ ግብረመልሶችን መሰረት በማድረግ የማስተካከያ ስራ በመስራት ለህጻናቱ ምቹ የመማሪያ ስፍራ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው ቢሮው በ2016 ዓ.ም 40 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ተግባራዊ አድርገው ትራንስፎርም እንዲሆኑ የተለያዩ ግብአቶችን ከማቅረብ ጀምሮ በርካታ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው በ2017 ዓ.ም በተመሳሳይ 60 ትምህርት ቤቶች በፕሮግራሙ መያዛቸውን በመጥቀስ የዛሬው መርሀግብር በነዚሁ 100 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተደረገ ምልከታን መሰረት አድርጎ በተዘጋጀ ግብረ መልስ ላይ ውይይት በማድረግ በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት ታስቦ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የቢሮው የቀዳማይ ልጅነት ጉዳዮች ቡድን መሪ ወይዘሮ ፍሬሕይወት በቀለ በቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቹ የተደረገ ምልከታን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ግብረ መልስ በዝርዝር አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል።

0 Comments