ስርአተ ጾታን መሰረት ያደረገ የማስተማር ስነ ዘዴን(Gender responsive pedagogy) በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ።

by | ዜና

(ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም) ስልጠናው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ትግበራ ቡድን የተሰጠ ሲሆን በመርሀ ግብሩ በየትምህርት ቤቱ የሚገኙ የስርአተ ጾታ ክበባትን የሚደግፉ ምክትል ርዕሳነ መምህራን እና የክበባቱ ተጠሪ መምህራን ተሳታፊ ሆነዋል።

አዲሱ ስርአተ ትምህርት የዘርፈ ብዙ ጉዳይን ትኩረት የሰጠ እንደመሆኑ በየትምህርት ቤቱ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው የመማር ማስተማር አገልግሎት የስርአተ ጾታ ጉዳይን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው መዘጋጀቱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ትግበራ ቡድን መሪ አቶ ይልማ ተሾመ አስታውቀዋል።

ቡድን መሪው አክለውም ስልጠናው በየትምህርት ቤቱ የተደራጁ የስርአተ ጾታ ክበባትን በማጠናከር ጾታን መሰረት አድርገው የሚስተዋሉ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያግዝ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመው ስልጠናው ከኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በዘርፈ ብዙና ቀዳማይ ልጅነት ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ በላይነሽ የሻው በበኩላቸው በትምህርት ፖሊሲው የተካተተው የስርአተ ጾታ ጉዳይ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን ለትምህርት ማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላክተዋል።

0 Comments