ለተቋማት የሚደረግ ድጋፍና ክትትል በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎችን በማየት በትምህርት ተቋማቱ የተሻለ የትምህርት ጥራትና የተማሪ ውጤትን ለማጎልበት ከፍተኛ ሚና እንዳለዉ ተገለጸ፡፡

by | ዜና

(ህዳር 3/2017 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት የ2017 በጀት ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀምና የተግባር ሥራዎች አጀማመር ዙሪያ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ስር ለሚገኙ የወረዳ ትምህርት ፅ/ቤቶች ፣1ኛ ደረጃ ፣ መካከለኛ ደረጃ እና አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና ለአዳሪ ት/ቤቶች ክትትልና ድጋፍ ለሚያደርጉ አካላት ኦረንቴሽን ሰጠ::

በኦረንቴሽኑ ላይ በመገኘት የስራ አቅጣጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አማካሪና የዘርፉ ኃላፊ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ የዝግጅት ምዕራፍ ለትምህርት ሴክተሩ ዋና ዋና ተግባራት የሚከናወንበት ወቅት መሆኑን ጠቅሰው ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በመጀመሪያ ምዕራፍ የተከናወኑ የቁልፍ አፈፃፀም አመላካች ሥራዎችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር እንዲሁም በ2016 ዓ.ም የታዩ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶችን ለማረም በሚያስችል መልኩ እቅድ መታቀዱንና እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የተሄደበትን ርቀት በድጋፍና ክትትሉ በሚደረግ ምልከታ እንደሚታይ ተናግረዋል ፡፡

አያይዘውም ክትትልና ድጋፉ በቅንጅታዊ ስራዎች የተሰሩ ሥራዎችን በማየት ቀጣይ የትምህርት ስራውን ስኬታማ ለማድረግ ከእቅድ ዝግጅት ጀምሮ ወደ ተግባር ምዕራፍ ለመግባት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም በሁሉም የትምህርት ተቋማት ተቀራራቢ አፈጻጸም እንዲኖር አቅም ለመፍጠር የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል:: ድጋፍና ክትትል የሚያደርጉ ባለሙያዎችም የድጋፍና ክትትል ስራው ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት በድጋፍና ክትትሉ ወቅት የሚታዩ ክፍተቶችን በሚያዘጋጁት ግብረ መልስ በግልጽ በማሳየት በትምህርት ተቋማቱ ቅማቸውን ለማሳደግና ቀጣይ ለሚደረግ የስራ ምዘና በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅም በመፍጠር ኃላፊነታችሁን በአግባቡ እንድትወጡ በማለት ሊከተሉ የሚገባቸውን የስራ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል::

የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋአገኘሁ ለገሰ በበኩላቸው ከማእከል እስከታች ወረዳና ትምህርት ቤቶች ድረስ ወርዶ የትምህርት አፈጻጸም ስራዎች በተመሳሳይ አሰራርና ወጥ የሆነ ስርዓት እንዲዘረጋ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት የነበሩ የክትትልና ድጋፍ ግብረመልሶች ለክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ቀርቦ ክትትል ድጋፍ ሲደረግ የቆየ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በቀጣይም በሚቀርቡ የድጋፍና ክትትል ስራ ግብረመልስ ውጤት ለወረዳ ስራ አስፈጻሚ ቀርቦ የድጋፍና ክትትል ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ በኦረንቴሽኑ ላይ ለተነሱ የግልጽነት ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

በኦረንቴሽኑ ላይ የሪፎርምና አገልግሎት አሰጣጥ ክትትል ድጋፍና ምዘና ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሃፍቱ ብርሃኔ የክትትልና ድጋፉን አስፈላጊነትና አላማ እንዲሁም ምንነትና ይዘቶች የያዘ ሰነድ አቅርበዋል ፤ በሰነዱም የድጋፍና ክትትሉ ባለሙያዎች ሊከተሉት የሚገባ የግብረመልስ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ላይ ማብራሪያ አቅርበዋል::

በዚህ ለሁለተኛ ጊዜ በሚደረግ ድጋፍና ክትትል ስራ ከቢሮ ፤ ከክፍለ ከተማ እና ከወረዳ የተውጣጡ 415 የሚሆኑ የመደገፍ አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ ባለሙያዎችና ሱፐርቫይዘሮች የሚሳተፉ ሲሆን በ 458 በሚሆኑ 1 ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ፤አዳሪ ትምህርት ቤቶችና የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤቶች በመገኘት ድጋፍና ክትትሉን እንደሚያደርጉ ከስራ ክፍሉ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

0 Comments