(ጥቅምት 22/2017 ዓ.ም) ስልጠናው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት አማካይነት ለክፍለ ከተማና ወረዳ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን የቢሮው የትምህርት አመራር አሰልጣኝ ባለሙያ አቶ አበበ ገስጥ በተከታታይ ሙያ ማሻሻያ (ተ.ሙ.ማ)መርሀ ግብር ዙሪያ ስልጠናውን ሰተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በስልጠናው መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ልማት ስራው የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ የሚችለው የመምህራንንም ሆነ የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም በማሳደግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ እንደመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ቡድን መሪዎችና ባለሙያዎች ተገቢውን የአቅም ግንባታ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አያይዘውም በ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ቢሮው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመረበት የተማሪዎችን የእንግሊዘኛና ሒሳብ ትምህርት ውጤት የማላቅ ስትራቴጂ በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን በትምህርት አይነቶቹ ለሚያስተምሩ መምህራን ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አድማሱ በበኩላቸው ዳይሬክቶሬቱ መምህራንን ከመመደብና የደረጃ እድገት እንዲያገኙ ከማስቻል ባሻገር በዕውቀት፣አመለካከትና ክህሎት ብቁ ሆነው የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር በአግባቡ ማሻሻል እንዲችሉ የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚሰጥ ገልጸው በተከታታይ ሙያ ማሻሻያ (ተ.ሙ.ማ) መርሀ ግብር ዙሪያ የተዘጋጀው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።
በተከታታይ ሙያ ማሻሻያ (ተ.ሙ.ማ) መርሀ ግብር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ።
0 Comments