በተሻሻለው የትምህርት ቤት ምገባ አሰራር ማኑዋል እና የምገባ አገልግሎቱን በተመለከተ በትምህርት ተቋማት በተደረገ የክትትልና ድጋፍ ግብረ መልስ ሪፖርት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

(ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም) መርሀ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የግብአት ፍላጎት አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት አማካይነት የተዘጋጀ ሲሆን በውይይቱ የትምህርት ቤት የምገባ ቁጥጥር ባለሙያዎችን ጨምሮ የክፍለ ከተማ የዘርፈ ብዙ ቡድን መሪዎችና የምገባ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር በመርሀግብሩ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የትምህርት ቤት የምገባ አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉ ለወላጆች እፎይታ ከመስጠቱ ባሻገር ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ጠቁመው በየትምህርት ቤቱ የተመደቡ የምገባ ቁጥጥር ባለሙያዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ተማሪዎቹ የምገባ አገልግሎቱን በተዘጋጀው ሜኑ መሰረት ጥራቱን ጠብቆ ማግኘት እንዲችሉ ተገቢውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ መስራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የቢሮው የትምህርት ግብአት ፍላጎት አቅርቦትና ስርጭት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን መለሰ በበኩላቸው ቀደም ሲል በየትምህርት ቤቱ ከሚገኙ መጋቢ እናቶች ጋር በምገባ አገልግሎቱ ዙሪያ ተመሳሳይ ውይይት መደረጉን ገልጸው በዛሬው ውይይት በአሰራር ማኑዋሉ ዙሪያ ከምገባ ቁጥጥር ባለሙያዎች የሚነሱ ገንቢ ሀሳቦች ተካተው በቀጣይ ማኑዋሉን በማጽደቅ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

በ2017 ዓ.ም የትምህርት አመት በሁሉም የመንግስት ቅድመ አንደኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን የቢሮ የተማሪዎች ምገባ ቡድን መሪ አቶ አለሙ ሀይሉ ጠቅሰው ከተማ አስተዳደሩ ለምገባ አገልግሎቱ 3.6 ቢሊየን ብር በጀት መመደቡንም አስታውቀዋል።

0 Comments