ቀን 17/3/2014 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በአፋር ክልል በአሸባሪው የህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ51 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል፡፡

ድጋፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ ለአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ ዛሬ በሠመራ ከተማ አስረክበዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር፤አሸባሪው የህወሃት ቡድን ሀገር ለማፍረስ ለዘመናት ሲዘጋጅ መቆየቱን አስታውሰዋል። ቡድኑ በሀገር ላይ የቃጣውን ጥቃት በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ የተፈጸመ መሆኑን አውቆ ሁሉም ዜጋ በአንድነት በመቆም ጠላቱን በመመከት ላይ ይገኛል ነው ያሉት። ይህም የአሸባሪው ቡድን ግብአተ-መሬት እስኪፈጸም ድረስ የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ለተፈናቃይ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ መቀጠሉንም አስረድተዋል።

ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ጊዜያት ተደጋጋሚ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚ መሆኑን በመጥቀስ፤በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው የአፋር ክልል ህዝብ የአሸባሪው ህወሃት ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራ በማክሸፍ ተጋድሎ ውስጥ በመሳተፍ ትውልዱ ሲኮራበት የሚኖር ታሪክ መስራቱን ተናግረዋል።

ለዚህ ጀግና ህዝብ በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ወገናዊ አጋርነታቸውን ለማሳየት ከ51ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ማበርከታቸውን አስታውቀዋል።

ድጋፉን ያበረከቱት የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ፣ የየክፍለ ከተማው የትምህርት ጽህፈት ቤቶች ፣የግልና መንግስት ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች፣መምህራንና ሌሎችም በትምህርት ዘርፍ የተሰማሩ እንደሆኑ አመላክተዋል።

ሀላፊዉ አክለዉም በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ አሸባሪው እስከሚደመሰስ ድራስ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

ለምግብነት የሚውል ዱቄት፣ ማካሮኒና ፓስታ፣ አልባሳትና የተለያዩ ንጽህና መጠበቂያዎች ከድጋፉ ውስጥ ይገኙበታል፡፡

Like
Like Love Haha Wow Sad Angry