ቀን 15 / 3/ 2014 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ማህበረሰብ አካላት 100 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን፣አልባሳቶች፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችን እና የንጽህና መጠበቂያዎችን ደብረ ብርሀንና ሰመራ ለሚገኙ ተፈናቃዮች አበረከቱ።

ድጋፉ የተበረከተው በሁሉም ክፍለ ከተሞች ከሚገ ኙ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች እና መምህራን እንዲሁም በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት ባለሙያዎችና አመራሮች ሲሆን ቁሳቁሶቹም በዛሬው ዕለት በ67 ኤፍ ኤስ አር የጭነት መጫኛ ተሽከርካሪዎች ተጭነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ፣ በምክትል ከንቲባ ማእረግ የፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ እና የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ነጂባ አክመል ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፣የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችና አባላትን ጨምሮ ተማሪዎች መምህራንና ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከመስቀል አደባባይ ወደ አከባቢዎቹ ተሸኝተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በሽኝት መርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ድጋፍ ከትምህርት ማህበረሰቡ በአንድ ሳምንት ውስጥ መሰባሰቡ በታሪክ ከፍ ብሎ የሚነገር ተግባር መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና በድል እንደምታልፈውና ቀጣዩ ትውልድም ነጻነቱዋና ክብሯ የተጠበቀ ሀገር እንሚተላለፍለት በመግለጽ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተርም ወደ ግንባር በመዝመት ለዚሁ ተግባር ህያው ማሳያ የሚሆን ግዳጅ ላይ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቱዋን አስከብራ የኖረች ታላቅ ሀገር መሆኑዋን እና በአሁኑ ወቅትም በአሸባሪው ህውሀትና በአንዳንድ የውጭ ሀይሎች የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ በልጆቿ የተባበረ ክንድ በመመከት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ የትምህርት ማህበረሰቦች ለሀገር አለኝታነታቸውን እና ለጠላት አልበገር ባይነታቸውን ደም በመለገስና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ በመጥቀስ በዛሬው ዕለት ወደ ሁለቱ አከባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚሸኘው ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን አስረድተዋል።

Like
Like Love Haha Wow Sad Angry