ቀን 23 /2/ 2014 ዓ.ም

የአዲ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው አዲስ አበባ ከሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች እና ወላጆች ጋር ውይይት አካሄደ።

ተማሪዎቹ ከሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው ፈተናውን አዲስ አበባ ለመፈተን ከሀገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲ አድሚሽን ካርድ ተልኮላቸው የተመዘገቡ ሲሆኑ በተጨማሪም በኮረና ቫይረስ ምክንያት ከሪያድና ጅዳ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ተፈታኞች በውይይቱ ተሳታፊ ሆነዋል።

በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ እንደገለጹት የ12ኛ ክፍል ፈተና ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ የህይወት ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት እንደመሆኑ ተፈታኞች አሁን የደረሰባቸው ችግር ሳይረብሻቸው ፈተናቸውን በተረጋጋ መንፈስ ውስጥ ሆነው መፈተን እንደሚገባቸው ጠቅሰው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹን በሚችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

የቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ በበኩላቸው ተማሪዎቹ ፈተናውን ዳግማዊ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ በተዘጋጀላቸው የመፈተኛ ጣቢያ እንደሚወስዱና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ቅዳሜ ጥዋት የፈተና ጣቢያ ተገኝተው የሚፈተኑበትን ክፍል እንደሚመለከቱ በመግለጽ በፈተናው ወቅት መታወቂያና አድሚሽን ካርድ ይዘው መገኘት እንደሚኖርባቸውም አስገንዝበዋል።

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ሐገራዊ ፈተና ከጥቅምት 29 እስከ ህዳር 2 ድረስ በመላው ሀገሪቱ እንደሚሰጥ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወቃል።

Like
Like Love Haha Wow Sad Angry