ቀን 16 /2/ 2014 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ክትትል ትግበራ ቡድን በኤች አይ ቪ ኤድስ ሜንስትሪሚንግ ዙሪያ ለት/ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጠ፡፡

በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ የትምህርት ሴክተር የትምህርት አካላትን በእውቀትና በስነ-ምግባር ከማብቃት ባለፈ ራሱንና ህብረተሰቡን ከኤች አይ ቪ ኤድስ ሊጠብቅ የሚችል ትውልድ ለማፍራት እንዲቻል እቅዶቻችን የሜንስትሪሚንግን ስራ ታች ድረስ የሚያደርሱ ሊሆኑ ይገባል ያሉ ሲሆን ችግሩን የጋራ በማድረግ እንደ ቢሮም ሆነ በግላቸዉም የኤች አይ ቪ ፈንድን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ ወ/ሮ ገንዘብ ደሳለኝ በስልጠናው ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በ2001 ዓ.ም የወጣ ደንብ ለውይይት ያቀረቡ ሲሆን የቢሮው ሰራተኛ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል፡፡

በቢሮው ድጋፍ ለሚደረግላቸው ህፃናት የአልባሳት ድጋፍና የኤች አይ ቪ ኤድስ ፈንድን ለመደገፍ የተለየ አስተዋፅኦ ላደረጉ 5 የቢሮው ሰራተኞች በምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ አማካኝነት የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

Like
Like Love Haha Wow Sad Angry