የትምህርት ጉባኤው  “በአዲስ ምዕራፍ አዲስ ተስፋ ለትምህርት ውጤታማነት እና ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን በጉባኤው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች ፣መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የወላጅ ማህበር ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በክብር እንግድነት ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ከተማ አስተዳደሩ በ2013 ዓ.ም ቅድሚያ ሰጥቶ ሲደግፋቸው ከነበሩ ሴክተሮች መካከል አንዱ የትምህርት ዘርፉ መሆኑን ገልጸው ሴክተሩም የተደረገለትን ድጋፍ በአግባቡ ተጠቅሞ ውጤታማ መሆኑን በመጥቀስ ለዚህ ውጤት መመዝገብ መምህራንን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው ከፍተኛ ምስጋና እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

ክብርት ከንቲባዋ አክለውም በትምህርት ሴክተሩ በ2013 ዓ.ም ከተከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ አዲሱን ስርአተ ትምህርት መሰረት አድርጎ የተዘጋጀውና በዚህ ትምህርት አመት በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍና የመምህር መምሪያ ሲሆን ከተማ አስተዳደሩ ስርአተ ትምህርቱ ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገባ ትምህርት ቢሮ በሚያከናውናቸው የተለያዩ ተግባራት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።

በትምህርት ጉባኤው ማጠቃለያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ አብረውት በጋራ ከሚሰሩ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር የትስስር ፊርማ በቢሮው ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ አማካኝነት የተፈራረመ ሲሆን በ2013ዓ.ም የትምህርት ዘመን በስራ አፈፃፀምና በተማሪዎች ውጤት የላቀ አፈፃፀም ያስመዘገቡ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለወረዳና ለክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤቶች እውቅና ከመሰጠቱ ባሻገር በ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል አፈጉባኤ ከክብርት ፋይዛ መሀመድ ተቀብለዋል።

Like
Like Love Haha Wow Sad Angry