አዲስ አበባ 1/13/2015 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 40 አመትና በላይ ላገለገሉ መምህራን እና የትምህርት አመራሮች ስለ አገልግሎታችሁ እናመሰግናለን በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር፣የአዲስ አበባ ከተማ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ድንቅአለም ቶሎሳን ጨምሮ የተለያዩ የክብር እንግዶችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት ዕውቅና ሰጠ።
የዕውቅና ፕሮግራሙ ጳጉሜን ለኢትዮጵያ በሚል በተያዘው መርሀግብር መሰረት በዛሬው እለት የተሰየመውን የአገልግሎት ቀን ምክንያት አድርጎ የተካሄደ ሲሆን ለአንጋፋ መምህራኖችና የትምህርት አመራሮቹ ጋቢን ጨምሮ ታብሌት ስልክ፣ሜዳልያና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዕውቅና መርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ለኢትዮጵያ ልዩ ስጦታ በሆነችው ጳጉሜ ወር ላይ ሆነን የአገልግሎት ቀን ብለን በሰየምናት እለት ለ40 አመትና በላይ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ዜጋን በዕውቀትና ስነምግባር ሲያንጹና ሲቀርጹ ለቆዩ አንጋፋ መምህራን ላበረከቱት አስተዋጽኦ በራሳቸውና በከተማ አስተዳደሩ ስም ምስጋና አቅርበው የመምህርነት ሙያ በየትኛውም የሙያ መስክ የተሰማሩ ባለሙያዎችን የሚያፈራ ሙያ እንደመሆኑ የሚገባውን ክብር መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በበኩላቸው በዛሬው የምስጋና መርሀ ግብር በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከ40 አመት በላይ ያስተማሩና በማስተማር ላይ የሚገኙ 153 መምህራን እና የትምህርት አመራሮች ዕውቅና እንደተሰጣቸው ጠቁመው የምስጋና መርሀግብሩ በትምህርት ልማት ስራው በቀጣይ የሚከናወኑ ተግብራትን ውጤታማ ለማድረግ መሰረት የሚጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመምህርነት ሙያ ትውልድን በመቅረጽ የሀገርን ሁለንተናዊ እድገት የሚያረጋግጥ ሞያ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር በምስጋና መርሀግብሩ ማጠቃለያ ገልጸው ከተማ አስተዳደሩ የመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብር እንዲያገኝ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።
0 Comments