የቢሮ ኃላፊዉ መልዕክት

መነሻ ገጽ E የቢሮዉ አስተዳደር E የቢሮ ኃላፊዉ መልዕክት

ዶክተር  ዘላለም ሙላት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ትምህርት ቢሮ ኃላፊ

ትምህርት ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ለመልካም አስተዳደር ማስፈን እና ለዘላቂ ልማት መፋጠን ቁልፍ መሳሪያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ትምህርት ይህንን ሚና በተገቢው ሊጫወት የሚችለው ጥራቱ ተጠብቆ ሲሰጥ እና ብቁ ዜጋ ማፍራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በሃገራችን የትምህርተ አቅርቦት ለሁሉም ዜጎች በፍትሃዊነት ለማዳረስ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ተነድፎ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውም ድህነትን ለማጥፋትና ሃገሪቱን በልማት ጎዳና ከተራመዱ ሃገሮች ተርታ ለማሰለፍ እንደ ሀገር የተቀመጠውን እራዕይ መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ማዕቀፍ አንፃር በከተማችን የተከናወኑ መጠነ ሰፊ ስራዎች ባለፉት ዓመታት የከተማችንን የትምህርት ተሳትፎና ፍትሃዊነት በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን የሚሰጠው ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን በማድረግ በሁሉም በጅምር ደረጃ የተሻሉ ውጤቶችን ማየት ተችሏል፡፡

ከተማችን የትምህርት ስራ በተደራሽነቱ እና በፍትሃዊነቱ ረገድ መሰረታዊ ለውጦች የታዩበት ቢሆንም በጥራቱ ረገድ ሰፊ ስራዎች መሰራት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ከዚህ መነሻ የአጠቃላይ የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ፓኬጅ ተቀርፆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ፓኬጁን መተግበር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የትምህርት አመራር የአመራር ብቃትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ስልጠናዎች መሰጠታቸው ፣ ለመምህራን ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት መስጠት የሚያስችላቸው የቅድመ ስራና የስራ ላይ ስልጠና መሰጠቱ ፣ ስርዓተ ትምህርቱ ከትምህርት ደረጃ የሚጠበቀውን ፕሮፋይል ሊያስጨብጥ የሚችል መሆኑም ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መሰራታቸው ፣ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በስርዓተ ትምህርቱ ተካቶ እንዲሰጥ መደረጉ ፣ የለውጥ መሳሪያዎች ማለትም BPR እና BSC ጥናት መሰረት በማድረግ አዲስ የትምህርት አደረጃጀትና አሰራር እንዲፈጠር በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣትና ተሞክሮን ለመለዋወጥ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው እንደዚሁም ይህን ለማጠናከር በክትትልና ድጋፍ ተግባራት እንዲታጀቡ ለማድረግ ጥረት መደረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሚጠበቀው አጠቃላይ ውጤት አንፃር ሲታይ የተመዘገበው ውጤት በቂ ነው ማለት አይቻልም፡፡

ስለዚህ ሃገራዊ ህዳሴ እውን የሚያደርግ ትውልድ እየተፈጠረ መሆኑን የሚያሳዩ ተስፋ ሰጪ ለውጦች መታየት በመጀመራቸው ይህንን ደግሞ የማስቀጠል ሃላፊነት የሁሉም የትምህርት ባለድርሻ ማለትም በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር ፣ መምህራን ፣ ተማሪዎች ፣ ወላጆች የግል ባለሃብቶችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሃላፊነት ስለሆነ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በጋራ እንረባረብ እላለሁ፡፡

ዶክተር ዘላለም ሙላት

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

ትምህርት ቢሮ ኃላፊ