የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በበይነ መረብ ኦን ላይን ለመስጠት እየተከናወኑ በሚገኙ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ ።

by | ዜና

(ቀን ሚያዚያ 22/ 2016 ዓ.ም) በውውይይቱ የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችን ጨምሮ የመንግስትና የግል ትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራን የተሳተፉ ሲሆን ውይይቱ ፈተናውን በበይነ መረብ ኦን ላይን ለመስጠት ከወዲሁ መከናወን በሚገባቸው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት  ዙሪያ ነው የተካሄደው።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በውይይቱ እንደገለጹት የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በከተማ አስተዳደሩ በበይነ መረብ ለመስጠት ከወዲሁ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው ፈተናው ኦን ላይን እንደመሰጠቱ ኮምፒውተሮች ፣ ላፕቶፖች እና ታብሌቶችን ጨምሮ ሎሎች አስፈላጊ  ግብአቶችን የማሟላት ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ኃላፊው አክለውም የግል ትምህርት ቤቶች ለፈተናው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን የማዘጋጀት ተግባራቸውን ከወዲሁ በመጀመር ፈተናው በታቀደለት መርሀ ግብር እንዲሰጥ የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከሀምሌ 3 እስከ 5 የማህበራዊ ሳይንስ  እንዲሁም ከሀምሌ 9 እስከ 11/2016 ዓ.ም የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና እንደሚሰጥ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ በትላንትናው እለት መግለጹ ይታወቃል።

0 Comments

SITE VISITORS

  • 0
  • 187
  • 249
  • 2,423
  • 8,975
  • 243,957
  • 243,957