(አዲስ አበባ 4/1/2016 ዓ.ም) ውይይቱ የ2016 ዓ.ም የትምህርት ማስጀመሪያ ሳምንትን መሰረት አድርጎ የተካሄደ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮም ከእቴጌ መነን የልጃገረዶች እና ገላን የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ከተውጣጡ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ ከማል በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት ሁለቱ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ውጤታቸውና በስነምግባራቸው የተሻሉ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመው በትምህርት ቤቶቹ የሚገኙ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተቋማቱ የተቋቋሙበት አላማ ስኬታማ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የቢሮ ኃላፊ አማካሪ አቶ ጥላሁን ፍቃዱ በበኩላቸው የ2016ዓ.ም የትምህርት ማስጀመሪያ ሳምንትን መሰረት በማድረግ በሁሉም ክፍለከተሞች ከመምህራን ጋር ተመሳሳይ ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸው ውይይቱ በዋናነት በ2015ዓ.ም የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና በሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን መሰረት በማድረግ በሚደረግ ውይይት መምህራን የሚጠበቅባቸውን ሚና በአግባቡ እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይ ነጋሽ የጋራ መግባባት ለውጤታማ መማር ማስተማር በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተካሂዷል።
0 Comments