”የጋራ መግባባት ለውጤታማ መማር ማስተማር! ” በሚል መሪ ቃል የ2016 ዓ.ም የትምህርት ማስጀመሪያ ሳምንት ውይይት ተካሄደ።

by | ዜና

በትምህርት ሳምንት ማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ፣የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፣የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውን ጨምሮ የክፍለከተማ እና ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች ፣ዋና እና ምክትል ርዕሳነ መምህራን፣ በየደረጃው የሚገኙ ሱፐር ቫይዘሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በውይይቱ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬው ውይይት በየደረጃው ከሚገኙ የትምህርት አመራሮች ጋር በ2015 ዓ.ም የነበሩ ጠንካራና በሂደት ባጋጠሙ ጉድለቶች ዙሪያ የጋራ አስተሳሰብ በመፍጠር የትምህርት ጥራት ጉድለቶችን ለመሙላት በሚያስችሉ ሀሳቦች በመወያየት የተሻለ ስራ ለመስራት ታስቦ መዘጋጀቱን ጠቁመው በነገው እለትም በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከመምህራን ጋር ተመሳሳይ ውይይት የሚካሄድ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶክተር ዘላለም አክለውም በ2016 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስርአትን በማስፈን ተማሪዎች ነፃና ፍትሀዊ የሆነ የትምህርት አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው የተማሪዎችን ውጤትና ስነምግባር ለማሻሻል በየደረጃው ያሉ የትምህርት አመራሮች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች ትውልድ የሚቀረጽባቸውና ሀገር የሚገነባባቸው ተቋማት እንደመሆናቸው ለየትኛውም የጸጥታ ስጋት ተጋላጭ እንዳይሆኑ እንዳይሆኑ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ጠቁመው በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢ ውስጥ የየትኛውም ፖለቲካም ሆነ ሀይማኖታዊ ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ አጀንዳዎችን ማራመድ እንደማይቻል ገልጸዋል።

በ2016 ዓ.ም ትምህርት ቤቶች ለየትኛውም የጸጥታ ችግር  ተጋላጭ እንዳይሆኑ የጸጥታ ሀይሉ ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ እና በጉዳዩ ተሳታፊ የሚሆኑ አካላት ከተገኙም በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ  የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውቀዋል።

በመርሀ ግብሩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ወንድሙ ኡመር የጋራ መግባባት ለውጤታማ መማር ማስተማር በሚል ርዕስ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ውይይት የተካሄደ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም 7  የ2016 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀመር በመድረኩ ተገልጿል።

0 Comments

Submit a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

SITE VISITORS

  • 0
  • 308
  • 374
  • 4,289
  • 15,619
  • 98,485
  • 98,485