ENGLISH                                                                                                                                                              የዌብሜይል     መልዕክት ይላኩልንየኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

የሕዝብ ግንኙነት ሙያ አለም አቀፍ መሰረትን ከጣለ አንድ ምዓተ ዓመትን እንዳስቆጠረ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ያገልፃሉ፡፡ ቀስ በቀስ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እንደ አንድ የትምህርት ክፍል ተወስዶ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዉስጥም እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ የሆነበት ዋንኛዉ ምክንያት ተፈጥሮአዊ መሆኑን ከግምት በማስገባት ሳይሆን የአስፈላጊነቱና እየሰጠ ያለዉ ጠቀሜታ ግንዛቤ እየሰረፀ መምጣት በመቻሉ ነዉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችንም የሙያዉ አስፈላጊነትና እየሰጠ ያለዉ ጠቀሜታ እየጎላ በመምጣቱ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት ይታያል፡፡ መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሳይቀሩ የህዝብ ግንኙነትን እንደ መረጃ ቋት በመጠቀም እድገታቸዉን እያፋጠኑበት ይገኛሉ፡፡

በተለይም ሀገራችን በተለያዩ መስኮች ልማትን ለማፋጠንና የእድገትና ማማ ለመቆናጠጥ ደፋ ቀና በምትልበት በአሁኑ ወቅት ሙያዉ የሚሰጠዉ አስተዋፅኦ የሚገደብ አይደለም፡፡ ሙያዉን መሳሪያ በማድረግ የአንድ ድርጅት አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለባለድርሻ አካላት ፣ ለህብረተሰቡ በማድረስ ምላሹን ተቀብሎ ይበልጥ መስራት የሚቻልበት መንገድን ያመቻቻል፡፡

የአዲስ አበባ ት/ቢሮም በሀገሪቱ የትምህርት ልማት እንዲፋጠንና የትምህርት ልማት ሰራዊት እንዲጎለብት ትልቁን ሚና እንዲጫወት ብቻ ሳይሆን ሃላፊነት ጭምር የተጠላበት ሴክተር ነዉ፡፡ ሴክተሩ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን በት/ቤት የሚገኙ ወጣቶች ዉጤታማ ሆነዉ እንዲቀረፁ ራዕይ ሰንቆና ተልዕኮ አመቻችቶ መንቀሳቀስ ግድ ይለዋል፡፡ እነዚህን ታዲያ ተግባራዊ የሚያደርገዉ ደረጃ በደረጃ የትኩረት መስኮችን ኢላማ አድርጎ ነዉ፡፡

ከላይ ለተቀመጡት እንቅስቃሴዎች መፋጠንና ዉጤታማነት የህዝብ ግንኙነት በተለያየ መልኩ ተግባራትን ይከዉናል፡፡ የተለያዩ የተግባቦት ስትራቴጂያዊ መለኪያዎችን ይጠቀማል፤ የተለያዩ የኮሙኒኬሽን አግባቦችን በመጠቀም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሴክተሩ በዓመት ሊሰራቸዉ ያስቀመጣቸዉን የትኩረት መስኮች ለማሳካት የተለያዩ የኮሙኒኬሽን አግባቦችን በመጠቀም በህብረተሰብና በሴክተሩ መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል፡፡

በሴክተሩ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመረጃ ሽፋን ፣ ጥራትና ተደራሽነትን በተፈለገዉ መልኩ ለማስኬድ፣ ዉስጣዊ ትስስርና የመረጃ መመጋገብ መፍጠር ወሳኝ ነዉ፡፡ መልካም ገፅታን ለመገንባት ፣ የህዝብን ተሳትፎ ለማሳደግ ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመቀነስ ፣ ቀልጣፋ ፣ ዉጤታማና ፍትሀዊ አገልግሎት ለመስጠት ከህዝብ ግንኙነት ጋር ያለዉ ትስስር ቀጣይነት ያለው ሊሆን ይገባል፡፡

የዉይይት መድረክና ሁነት በማዘጋጀት እያንዳንዱ የስራ ሂደት ዘርፉን አስመልክቶ የግንዛቤና የህዝብ ንቅናቄ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ማካሄድ አለበት፡፡በዚህን ወቅት ነዉ የህዝብ ግንኙነት ሀሳቡን የሚያበረታታዉ ፣ ሁኔታዎችን የሚያመቻቸዉ ‹‹ሜዳዉም ፈረሱም ይኸዉ›› ቀጥሉበት ብሎ የኮሙኒኬሽን አግባብን የሚጠቀመዉ፡፡ ከዚህ ባለፈ ዘመኑ የወለዳቸዉ የለዉጥ መሳሪያዎች BPRና BSCን ደግሞ ይበልጥ በመቀናጀት ፣ በመመጋገብና በመደጋገፍ መስራት እንደሚያስፈልግ ያበረታታል፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግ የትምህርት ስራ ዉጤታማ እንዲሆን ዉጤታማ ትዉልድ በት/ቤቶቻችን እንዲቀረፁ የመረጃ ልዉዉጣችንን ወደ ላቀ ደረጃ ልናደርስ ግድ ይላል፡፡

የመነሻ ሀሳብ ዓላማ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ደጋፊ የስራ ሂደትና ሌሎች ከት/ቢሮዉ የሚገኙ የስራ ሂደቶች የመረጃ ልዉዉጥ እና መመጋገብ ባህላቸዉ ዳብሮ ቀልጣፋና ዉጤታማ የመረጃ ፍሰት ሥርዓት በመዘርጋት የሕዝብና መንግስትን ፍላጎት ያማከለ ትምህርታዊ የመረጃ ጥማታቸዉን ለማርካት ነዉ፡፡

የግንኙነት አስፈላጊነት

የዚህ ፅሁፍ በዚህ ደረጃ ተጠናክሮ መቅረብ አስፈላጊ የሆነዉ መስረፅ ያለባቸዉ አዎንታዊ ሃሳቦች በመኖራቸዉ ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ ደግሞ በስራ ሂደቶች መካከል የነበረዉን የተንዛዛ የመረጃ ፍሰት በምልሰት ማየት እንዲቻልና እርስ በርስ ያለመናበብ ነግሶ እንደነበር መገንዘብ እንዲቻል ነዉ፡፡ በመጨረሻም ለዉጥ አራማጅ ፣ ልማትና እድገትን የተቀኘ የመረጃ ግብአትን በትምህርት መስኩ ናኝቶና ራዕይ እዉን ሆኖ እንዲታይ የሚያደርግ የመረጃ ልዉዉጥ በስራ ሂደቶች መካከል የመፍጠር አስፈላጊነትን ለማስገንዘብ ይሆናል፡፡

ከኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ደጋፊ የስራ ሂደት ምን ይጠበቃል?

የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ደጋፊ የስራ ሂደት የሚጠበቅበትን ለዉጥ በዉጤት ተተርጉሞ እንዲታይና የተፈለገዉ ስኬት እዉን እንዲሆን ግብአትን ማግኘት ግድ ይለዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለስራዉ ቀልጣፋነትና እመርታ የሚከተሉትን ግብአቶች ሊጠቀም ወይም ሊያገኝ ይገባል፡፡

 1. በጉዳዩች ላይ የመንግስት መረጃዎችን፣ ፓሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችን፣ እቅዶችን፣ የእቅድ አፈፃፀሞችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ከዋነኛ ምንጩ በፍጥነት የማግኘት ፍላጎትና ለመንግስት የማሳወቅ ፍላጎት፣
 2. ከሌላዉ አካል በመማር ራስንና አካባቢን የመለወጥ ፍላጎትንና
 3. የታቀደና በህዝብ ፍላጎትና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ስልጡን የመረጃ ፍሰት የመፍጠር ፍላጎት ናቸዉ፡፡

የሚጠበቁ አንኳር ተግባራት ፡-

 • ፕሬስ ሪሊዝ፣ የምስልና ድምፅ ቀረፃ፣
 • ፕሬስ ኮንፈረንስ፣ መጽሔት፣
 • ፈጣን ምላሽ፣ ኒዉስ ሌተር፣
 • ሁነቶችን ማደራጀት፣ በራሪ ወረቀት ዝግጅት፤
 • የዉይይት መድረክ ዝግጅት፣ የመንግስት ዜናዎችዝግጅት፣
 • የጉብኝትና ተሞክሮ ልዉዉጥ ዝግጅት፣ የአዳራሽ ፎቶ ግራፍና ኤግዚብሽን፣
 • የመስኮት ፎቶ ግራፍ ዝግጅት ኤግዚብሽን፣
 • የአርካይብ ዶክመንቴሽንና ስርጭት አገልግሎት ናቸዉ፡፡

ከስራ ሂደቶች ምን ይጠበቃል?

የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ደጋፊ የስራ ሂደት በቂ ግብአት፣ ዉጤትና ስኬትን ማግኘትና መቀዳጀት የሚችለዉ በተለያዩ መንገዶች ከሌሎች የስራ ሂደቶች የማያቋርጥ ወቅታዊና ቀጣይነት ያለዉ የመረጃ ፍሰት ሲደረግለት ብቻ ነዉ፡፡

በመሆኑም በት/ቢሮዉ የሚገኙ የስራ ሂደቶች ለታለመዉ ራዕይ መሳካት የሚከተሉትን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 1. ፕሬስ ሪሊዝ  ማዘጋጀት እንዲቻልና በሚዲያዎች አማካኝነት ለህዝብ እንዲደርሱ የስራ ሂደቶች በየሳምንቱ የሰሯቸዉን አንኳር ስራዎች ሪፖርት ግልባጭ ማድረግ፣
 1. ፕሬስ ኮንፈረንስ  አዘጋጅቶ በህብረተሰቡ ዉስጥ ንቅናቄ መፍጠር በሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዩች ዙሪያ የስራ ሂደት ባለቤቶች ርእስ በመምረጥ የሚዲያ ሰዎች እንዲጋበዙ ጥያቄ ማቅረብ፣
 1. ለቃለ ምልልስ  በግንባር ርዕሰ ጉዳይን በመለየት ማብራሪያ ተጠይቀዉ መስጠት ብቻ ሳይሆን የሚድያ ሰዎች እንዲጋበዙላቸዉ በማድረግ ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል፣
 1. ወርክሾፖች ሰሚናርና ሌሎች ሊደረጉ የታሰቡ እንቅስቃሴዎች ከመከናወናቸዉ ከሶስትና አራት ቀናት በፊት ለስራ ሂደቱ ማሳወቅ፤ ይህም ከሚዲያዎች ጋር ፕሮግራም ለመያዝ እድሉ የሰፋ ይሆናል፣
 1. በአዳራሽ የሚካሄዱ ማናቸዉም ፕሮግራሞች ቀደም ብሎ በስራ ሂደቱ ፕሮግራም ለማስያዝ ማሳወቅ ይጠበቃል፣

ተናቦ አለመስራት የሚያስከትለዉ አሉታዊ ገፅታ

በተፈለገዉና በስራ ሂደቶች መካከል የመናበብና የመመጋገብ የመረጃ ፍሰት ያለመኖር የሚያመጣዉ ወይም የሚያስከትለዉ አሉታዊ ገፅታ ይኖራል፡፡ እንደ አብነት የሚከተሉትን መጥቀስ ለግንዛቤ በቂ ነዉ፡፡

 • ወደ ቀድሞዉ አሰራር “AS IS ” እንደመመለስ ነዉ ፣
 • የመረጃ ፍሰት ቀልጣፋ ደንበኛን መሰረት ያደረገ አይሆንም፣
 • በመናበብ ስለማይሰራ ዉጤቱ አመርቂ አይሆንም፣
 • የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደቱ የሚጠበቅበትን መፈፀም ይሳነዋል፣
 • የሌሎች የስራ ሂደቶች ስራ “የጋን ዉስጥ መብራት” ይሆናል፡፡ ስራቸዉ ለህብረተሰቡ ደርሶ ግብረመልስ የሚያገኙበት አጋጣሚ አይኖርም፡፡

ማጠቃለያ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ት/ቢሮ የኮሙኒኬሽን ጉዳዩች ደጋፊ የስራ ሂደት በቢሮዉ ዉስጥ ከሚገኙ የስራ ሂደቶች ጋር ያለዉ ግንኙነት ምን ይመስል እንደነበር በምልከታ ዳብሮ እንዴት በመመጋገብ መጓዝ እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡ ይህም ት/ቢሮዉ ካስቀመጠው ራእይ ለመድረስ የሚያበረክተዉ አስተዋፅዎ ከዚህ በመለስ ብሎ ማስቀመጥ አይቻልም፡፡

ስለዚህ የታለመዉን ራዕይ ለመቀዳጀትና ደንበኛን ለማርካት ኃላፊነትን በብቃትና በተቀላጠፈ አካሄድ ለማሳካት ተልዕኮዎቻችንን በጥቅልና በወል ምን እንደሚጠበቅብን በመገንዘብ ከኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ጋር በመመጋገብ እና በመደጋገፍ በመስራት ፈጣን ለዉጥ ማምጣት ይቻላል፡፡