(አዲስ አበባ 24/1/2016 ዓ.ም) የአዲስ አበባ ከተማ አተዳደር ትምህርት ቢሮ ሰራተኞች የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት መድረክ አካሂደዋል፡፡ በመድረኩ ኢሬቻ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት እና የወንድማማችነት የምስጋና በዓል መሆኑ ፤ የኦሮሞ ሕዝብ የክረምቱን የጨለማ ጊዜ አሳልፈኸን ብራን ልምላሜን ውበትን ያሳየኸን፤ ተፈጥሮን ሕይወትን መልሰህ ያጎናፀፍከን፤ መሬቱን በልምላሜ፣ ድፍርሱን በጥራት የተካህልን፤ ወደ ብርሃንና መልካም ዘመን ያሻገርከን ፈጣሪያችን ምስጋና ይገባሃል በማለት ምስጋናውን የሚያቀርብበት እና ላጠፋነው ነገር ሁሉ ይቅር በለን እያለ ከፈጣሪው ጋር ጥልቅ ተፈጥሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ግንኙነቱን የሚያጠናክርበት በዓል እንደሆነ ተገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ በዓሉ የኦሮሞ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ መገለጫ እና በገዳ ሥርዓተ ትውፊት አማካኝነት ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ ድንቅ በዓል እንደሆነ የገለጹ ሲሆን በሁሉም ኢትዮጵያን የሚከበር በዓል ነው ብለዋል፡፡
በቢሮ ጽፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሲሳይ እንዳለ ኢሬቻ የአብሮነት የፍቅርና የይቅር ባይነት ተምሳሌት ነው ያሉ ሲሆን ፤ በዓሉን ስናከብር በፍቅር፣ እርስ በእርስ በመተሳሰብ፣ ለዘላቂ ሰላማችን የማረጋገጥ ሥራችንን እያጠናከን ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
የኢሬቻ የፓናል ውይይት መድረክ በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ተጀምሮ ለቀድሞ የትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ ለነበሩት ለአቶ አድማሱ ደቻሳ ፣ ለቀድሞ ለለሚ ኩራና ለኮልፊ ቀራኒዩ ክፍለ ከተማ ት/ጽ/ቤት ሀላፊዎች የሽኝት መርሀ-ግብር በማድረገና በምርቃት እንዲጠናቀቅ የተደረገ ሲሆን የመወያያ ሰነዱ በአቶ ፀጋዬ ሁንዴ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
0 Comments