በውይይቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የማኔጅመንት አባላትን ጨምሮ የምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን፣የደንብ ማስከበር ባለስልጣን፣የንግድ ቢሮና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አመራሮች፣ የተማሪ ወላጅ ማህበር ተወካዮች፣ የመምህራን ማህበር ስራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ተማሪዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በውይይቱ መክፈቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ቤቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚገነቡባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን ጠቁመው እነዚህ ተቋማት የሚፈለገውን የትውልድ ግንባታ ሂደት በአግባቡ እንዳይወጡ በአንዳንድ ኃላፊነት በጎደላቸውና የሞራል ልዕልና በሌላቸው ህገወጥ አካላት ለተለያዩ አዋኪ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኃላፊው አክለውም በትምህርት ቤቶች አከባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ተግባራትን ለመከላከል የተለያዩ ተቋማት በጋራ ተናበው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የመማር ማስተማር ስራው ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ መሆኑን ገልጸው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ሰሞኑን ትምህርት ቤቶች ከአዋኪ ተግባራት የጸዱ እንዲሆኑ እየወሰደ የሚገኘው እርምጃ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን በመጥቀስ የዚህ ውይይት ተሳታፊ ባለድርሻ አካላትም ችግሩን ለመቅረፍ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው የዛሬው ውይይት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በችግሮቹ መንስኤዎች ዙሪያ ፊት ለፊት ተወያይተው የተለያዩ የመፍትሄ ሀሳቦችን እንዲያስቀምጡ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በትምህርት ተቋማት የሚታዩ አዋኪ ተግባራት በትውልድ ግንባት ስራው የሚያስከትሉትን ተጽኖ ለመከላከል የሚያስችሉ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞችን መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በመርሀ ግብሩ በደንብ ማስከበር እና በምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በትምህርት ቤት አከባቢ ያሉ አዋኪ ተግባራት እያደረሱ የሚገኘውን ችግር የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን በዋናነትም ጫት ቤቶች ፣ሺሻ ማስጬሻዎች፣መጠጥ ቤቶች፣የተለያዩ ትምባሆና አደንዛዥ እጽ መሸጫ ቦታዎች እና ሌሎች መሰል ተግባራት በመማር ማስተማር ስራው ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ ለመፍትሄው በጋራ መስራት እንደሚጠበቅበት በጽሑፍ አቅራቢዎቹ ተገልጿል።